ቀጥታ፡

በሪፎርሙ ሰላምና ደህንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅና ህዝብን የሚያገለግል ፖሊስ ተገንብቷል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ በሪፎርሙ ሰላምና ደህንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅና ህዝብን የሚያገለግል ፖሊስ መገንባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የ24ኛ ዙር መደበኛ እጩ ሰልጣኝ መኮንኖች የምረቃ መርሀ ግብር አካሂዷል።


 

እጩ መኮንኖቹ የህገ-መንግስትና ሰብዓዊ መብት፣ ግጭት አፈታት፣ የፌደራሊዝምና ወንጀል መከላከያ እና መሰል አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን በብቃት የተወጡ ናቸው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፣ ከለውጡ በፊት የነበረው የመንግስት አሰራር ነባሩን በማፍረስ ከዜሮ የመጀመር ነበር።

የለውጡ መንግስት በሪፎርም ስራዎች የጎደለውን በመሙላት ተደማሪ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሪፎርም ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አንስተዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።

በጸጥታ ተቋማት ላይ የተደረገው ሪፎርም፤ ቴክኖሎጂ መር እና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለም ገልጸዋል።

የዛሬ ተመራቂ እጩ የፖሊስ መኮንኖችም በሙያቸው ቅን እና ታማኝ በመሆን ፖሊሳዊ ስነምግባርን በተግባር ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡


 

በስልጠናው ያገኙትን አቅም ለላቀ ህዝባዊ አገልግሎት በማዋል ለከተማዋ ሰላምና ልማት አጋዥ እንዲሆኑም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የከተማዋን እድገት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

እጩ ሰልጣኝ መኮንኖች የተሰጣቸውን የንድፈ ሀሳብ ስልጠናዎች በብቃት መወጣታቸውንም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ከጸረ- ሰላም ኃይሎች መጠበቅ መቻሉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም