ቀጥታ፡

ለመጪው አዲስ ዓመት የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከውጭ ሀገር ዘይት በመግዛት እየተሰራጨ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ ለመጪው አዲስ ዓመትና ቀጣይ በዓላት የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከውጭ ሀገር ዘይት በመግዛት እያሰራጨ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለፀ።

ለመጪው አዲስ ዓመትና ለቀጣይ በዓላት 63 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ምርቶችን ከውስጥና ከውጭ አምራቾች በመግዛት ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው።

መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች (ዘይት፣ ስኳር፣ የስንዴ ዱቄት) የታሸጉ ምግቦች፣ የተለያዩ ለስላሳ መጠጦች፣  የቤትና የግል ንጽህና መጠበቂያዎችና የጽህፈት መሳሪያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ለመጪው አዲስ ዓመትና ለቀጣይ በዓላት የምግብ ዘይት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከውጭ ሀገር በመግዛት ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ 63 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ የሱፍ እና የፓልም የምግብ ዘይት ከውጭ ሀገር በመግዛት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ ነው ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ በዛሬው ዕለት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትሩ በአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኘው እንዶዴ ባቡር ጣቢያ መድረሱንና አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ክልሎች እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም በበዓል ወቅት የሚከሰተውን የዘይት ምርት አቅርቦት በመቅረፍ ገበያውን እንደሚያረጋጋ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ምርቶቹን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ሸቀጦች ግብይት ማዕከላትና በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች  በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም