ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዕምቅ የቱሪዝም ኃብት በአግባቡ ለመጠቀም ዕውቀትና ስብዕናን የተላበሰ ሙያተኛ ማፍራት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያን ዕምቅ የቱሪዝም ኃብት በአግባቡ ለመጠቀም ዕውቀትና ስብዕናን የተላበሰ ሙያተኛ  በብዛትና በጥራት ማፍራት እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሦስት ዓመታት ያሰለጠናቸውን 478 ሰልጣኞች አስመርቋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እየለሙ ያሉ የቱሪዝም ኃብቶች ዕውቀትና ስብዕናን የተላበሰ ሙያተኛን በብዛት ይፈልጋል።

 ዘርፉ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት የጎደሉ ነገሮች ተሟልተው ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም እንዲሰጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የዛሬው ምሩቃን ለዘርፉ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸው፤ በሙያቸው ሁለንተናዊ ስብዕናን በመላበስና በታማኝነት በማገልገል ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።   

ዘርፉን ለማዘመን ወሳኙ የሰው ኃይል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሀገር በቀል እውቀቶችን ሳንጥል ዘርፉ ያመጣቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አክለን መሄድ ይኖርብናልም ነው ያሉት።

ሰልጣኞች በዘርፉ በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር ታጥቀው አገር የሚያስተዋውቁበት በመሆኑ በታማኝነት በማገልገል ሚናቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሆቴልና ቱሪዝም የሥልጠና ፕሮግራም በመከታተል በዛሬው ዕለት ለምረቃ እንዲበቁ  ገልፀዋል።

ምሩቃኑ በዲግሪ መርኃ-ግብር በሆቴልና በቱሪዝም ማኔጅመንት እንዲሁም  በደረጃ ሦስት በምግብና መጠጥ መስተንግዶ፣ በቱር ጋይድ፣ በምግብ ዝግጅትና በቱሪዝም ማርኬቲንግ የሰለጠኑ  478 ሰልጣኞች ናቸው ብለዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 172 ወንዶች ሲሆኑ፤ 306 ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል። 

በተጨማሪም በተቋሙ ውስጥ  30 አነስተኛ የደመወዝ ተከፋይ የተቋሙ ሠራተኞችን በማሰልጠን ተጨማሪ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበትን ዕድል አመቻችቶ በዛሬው ዕለት ማስመረቅ መቻሉንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ በተማሩበት የሙያ መስክ አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ ሰልጥነው ወደ ሥራ መግባታቸው ዘርፉን ለማዘመን አቅም እንደሚሆን ነው የገለጹት። 

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተማሪዎችን በዘርፉ አሰልጥኖ ሲያስመርቅ ይህ ለ56ኛ ጊዜ ነው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም