የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ከትምህርት ተቋማት ጋር በማቀናጀት የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ከትምህርት ተቋማት ጋር በማቀናጀት የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ተግባር እየተከናወነ ነው
ጅማ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ):- የአቪየሽን እንዱስትሪውን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በማቀናጀት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአቪዬሽንና የህዋ ሳይንስ የስልጠና መርሃ ግብር መስጠት ሊጀምር መሆኑም ተገልጿል።
ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተቋማቱ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአቪዬሽን ሳይንስ አካዳሚው በይፋ ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ጌታቸው መንግስቴ በወቅቱ እንደገለፁት፤ መርሃ ግብሩ ከትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዘርፉን በሰው ሀይል ለማጎልበት ያግዛል።
የአቪዬሽን ሳይንስ የስልጠና መርሀ ግብር ከተቋሙ ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሊሰጥ ስምምነት ላይ ተደርሶ በይፋ የተከፈተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪው ሰፊና የሰለጠነ የሰው ኃይልን የሚፈልግ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በውስጡም የአቪዬሽንና የህዋ ሳይንስን ያጠቃለለ ነው ብለዋል።
ዘርፉን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በስልጠና የሰው ኃይል ፍላጎትን ለማሟላትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ስልጠናው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጋር በቅንጅት መሰጠቱ ኢንዱስትሪውን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ እና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የዘርፉ ተቋማት ጋር በመተባበር የአቪዬሽን ሳይንስና የኤሮ-ስፔስ ኢንጂነሪንግ አካዳሚ መከፈቱን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው አካዳሚውን ለመክፈት ካቀደ የቆየ ቢሆንም ለሁለት ዓመት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ ላይ እውን ሊሆን መቻሉ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።
የአቪዬሽንና የኢሮ-ስፔስ ኢንጂነሪንግ አካዳሚን በመክፈቱ ሂደት የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ የአየር ኃይልና የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ አራት መደበኛ የትምህርት መርሀ ግብሮችና ሁለት የእስፔሻላይዜሽን ኮርሶች የሚሰጡ ሲሆን በቀጣይ ሴሚስተርም መሰጠት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የባለስልጣኑና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።