ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት በማረጋገጥ እንዲገበያይ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ ለዘመን መለወጫ በዓል የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት በማረጋገጥ እንዲገበያይ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አሳሰበ።

ኢትዮጵያውያን በደማቅ ሁኔታ ከሚያከብሯቸው በዓላት መካከል የዘመን መለወጫ አንዱ ሲሆን ለበዓሉ የተለያዩ ምግብና መጠጥ አይነቶችን መስራት የሚያስችላቸውን ምርቶችን ይገበያያሉ።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የምግብ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ፤ ህብረተሰቡ የዘመን መለወጫ በዓልን ለማክበር ምርቶችን እየተገበያየ ይገኛል ብለዋል።

ይህንንም ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱና ህጋዊ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን ምርቶች ለመሸጥ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ለበዓል የሚገበያቸውን የምግብና መጠጥ ምርት ጥራትና ደኅንነት በማረጋገጥ ሊገዛ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለዚህም ግብይት በሚፈጽምበት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ካሉ በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት ወንጀለኞችን ማጋለጥ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሚከበሩ በዓላትን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ በመሸጥ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

ከዘመን መለወጫ በዓል ጋር ተያይዞ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም ከተፈጸመም ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የግብይት ሂደቱን ተጠቅመው ለወንጀል ተግባራት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በመከታተልና በመቆጣጠር በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም