ቀጥታ፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተተገበረው ሪፎርም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መሰረት የጣለ ነው-የትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተተገበረው የሪፎርም ስራ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መሰረት የጣለ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም  የሪፎርም ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት”በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።

እንደ ሀገር የፖሊሲ ሪፎርም ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ ለዓመታት በውስብስብ ችግሮች ውስጥ የቆየው የትምህርት ዘርፍ ነው።

የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ካተኮረባቸው ጉዳዮች መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአሰራርና የትኩረት መስክ ለውጥ ይገኝበታል።

የትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ላይ ሰፋፊ ለውጦች ተካሄደዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎርም ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል የፈተና አሰጣጥ፣ ተልዕኮና የትኩረት መስክ፣ የትምህርት ተገቢነት፣ የስርአተ ትምህርት ለውጥ እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

ከተካሔደው የሪፎርም ስራ ውስጥ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ዋንኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

በዋናነትም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተካሔደው ሪፎርም የትምህርት ጥራትንና ተገቢነትን ለማምጣት አስችሏል ነው ያሉት መሪ ስራ አስፈጻሚው።

ሪፎርሙ  በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት የንድፈ ሀሳብና የተግባር እውቀት እንዲገበዩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በአዲሱ አሰራር የተማሪዎች ብቃትና ክህሎት የሚለካ የመመዘኛ ስርዓት እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መምሕራን ማሕበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት  የትምህርት ፖሊሲው መሻሻሉ ለውጥ አስገኝቷል ብለዋል።


 

በዘርፉ የተካሔደው ሪፎርም በመምህራን ልማት፣ በትምህርት ቤቶች ማሻሻያ፣ በግብዓት አቅርቦትና የምገባ አገልግሎት ዘርፉን ለማሻሻል ያስቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሪፎርሙ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትኩረት መስክ ልየታ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማዊ ነጻነት እንዲሁም ለተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መስጠትን ወደ ተግባር የማስገባት ስራ ተጀምሯል።

የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በጥናት ላይ በመመስረት የምርምር፣ የተግባር፣ የአጠቃላይ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የትምህርት በሚሉ አምስት ዘርፎች የመደልደል ስራ ተከናውኗል።

የመውጫ ፈተናም ከ2015 የትምህርት ዘመን ማጠናቀቂያ ጀምሮ በሁሉም የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተሰጠ ሲሆን፥ ይህም ብቃት ያላቸው ተመራቂዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል እምነት ተጥሎበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም