የመከላከያ ሠራዊት በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ሐረር፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ):- የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸምና ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ የተመሰረተበትን 47ኛ ዓመት በዓል በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲየም እየተከበረ ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ የመከላከያ ሰራዊት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸምና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል።
የሰራዊቱ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ተልዕኮውን በብቃት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ሕልውናና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ምስራቅ ዕዝ በእሳት የተፈተነና ለሀገር ሉዓላዊነት አኩሪ ጀግንነት የከፈለ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተጀመረው ሀገር የማፅናትና የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በፈጣን የእድገት ጉዞ ላይ ትገኛለች ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ይህ የልማት ጉዞ እንቅልፍ የነሳቸው ፀረ ሰላም ሃይሎች የውስጥ ባንዳ ቀጥረው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ከዚህ ተግባርም እንዲታቀቡ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዓሉ በተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶች እየተከበረ ይገኛል።