ባለፉት ስድስት ዓመታት የሕግ፣ የአሰራር፣ የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጦች ብሎም ተቋማት ሪፎርም በመደረጋቸው አበረታች ውጤቶች ታይተዋል- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ዓመታት የሕግ፣ የአሰራር፣ የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጦች ብሎም ተቋማት ሪፎርም በመደረጋቸው አበረታች ውጤቶች ታይተዋል- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ዓመታት የሕግ፣ የአሰራር፣ የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጦች ብሎም የተቋማት ሪፎርም በመደረጋቸው አበረታች ውጤቶች መታየታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገዕልግሎት ለጳጉሜን 2፣ የሪፎርም ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል
እንኳን ለጳጉሜን 2፣ የሪፎርም ቀን አደረሳችሁ!-
ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ/ም፣ የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ይውላል፡፡
እንደ ሀገር ያጋጠሙንን የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ስብራቶቻችንን ለመጠገንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ባጠረ ጊዜ ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች ተጀምሯል፡፡ ውጤቶችም ተመዝግበዋል፡፡ በተለመዱ አሰራሮች፣ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ተቋማት የምንፈለገውን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለሆነም በሁሉም መስክ የሪፎርም እርምጃዎች ተወስዷል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት የሕግ፣ የአሰራር፣ የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጦች ብሎም የተቋማት ሪፎርም በመደረጋቸው አበረታች ውጤቶች ታይቷል፡፡
በለውጥ ዓመታት ከተደረጉት የተቋማት ሪፎርም አንዱ የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም ነው፡፡ በቀደመው ሥርዓት የዴሞክራሲ ተቋማት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ከማስከበር ይልቅ የአንድን ቡድን ጠባብ ፍላጎት ለመጠበቅ የተደራጁ የይስሙላ ተቋማት ነበሩ፡፡
በመሆኑም የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ በመመለስና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ያጋጠመን የፖለቲካ ስብራታችንን ለማረም እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ሪፎርም ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳን የነፃነትና ገለልተኝነት አረዳድና ልምምድ ገና ቢሆንም ተቋማቱ ከመንግስት ጫና ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነው ሥራቸውን ማከናወን ጀምሯል፡፡
በተጨማሪም ለዘመናት የፖለቲካ ሥርዓት ጠባቂና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስከባሪ ተደርጎ የተዋቀሩ የፀጥታ ተቋማት ከፖለቲካ ነፃ ሆነው እንዲደራጁ፣ የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ጠባቂ እንዲሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲና የአደረጃጀት ሪፎርም ተደርጓል፡፡ በዚህም አስተማማኝና ጠንካራ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መከታ የሆኑ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት እንዲሁም የመረጃና ደህንነት ተቋማት ተገንብተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከባለፉ ሥርዓቶች የወረስናቸው የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአሰራራቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸው ውስብስብና ቀርፋፋ በመሆናቸው ለሕዝባችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት መልስ መስጠት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ የተለያዩ የሪፎርም እርምጃዎች ተወስዷል፡፡ በአንድ በኩል ተቋማቱ በአደረጃጀታቸው እና አሰራራቸው ተለውጠው ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሸያ ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ በሚቀጥለው አዲስ ዓመት የመንግስታችን ዋና የሪፎርም ትኩረት መስክ ሆነው ይቀጥላል፡፡
በሌላ በኩል ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጣቸው እንዲዘምኑ ለማድረግና ከንክኪ ለማራቅ የተለያዩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኢንሼቲቭ ተጀምሯል፡፡
ከዚህ አንፃር “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ኢንሸቲቭ” ተቀርፆ ወደ ትግባራ ተሸጋግሯል፡፡ ተስፋ ሰጪ ስኬቶችም ተመዝገበዋል፡፡
በምንቀበለው አዲሱ ዓመትም ተጠናክረው ይቀጥላል፡፡
ሀገራችን ያጋጠማትን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሪፎርም ቀርፆ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ በዚህም ሀገርን የታደገ ውጤት ተገኝቷል፡፡
እየተገባደደ ባለው ዓመት መጨረሻም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አካል የሆነው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሸያ አድርጓል፡፡
የፖሊሲ ማሻሸያው የሀገራችን የኢኮኖሚ ስብራት በመጠገን በሂደት የኑሮ ውድነትና የእዳ ጫናን ለመቀነስ፣ የክፍያ ሚዘን መዛባት ችግሮችን ለመፍታት፣ የበጀት ጉድለትን ለማስተካከልና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ዓይነተኛ መፍትሔ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሸያው እንዲሳካ የሀገር ውስጥ ገቢና ቁጠባን ማሳደግ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም የተጀመሩ የተቋም ሪፎርም ሥራዎች፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሸያዎች እና ሌሎች የሪፎርም ስራዎቻች እንዲሳኩ ለማድረግና መግባባት ላይ ለመድረስ ጳጉሜ 2 የሪፎርም ቀን ተብሎ ተሰይሟል፡፡
በአዲሱ ዓመት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተሰማራበት የሥራ መስክ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ሃላፊነት በመወጣት ለሁለንተናዊ የብልጽግናችን ጉዞ ለማፋጠን የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በቁርጠኝነትና የሃላፊነት ስሜት ከግብ እንዲያደርሱ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
መልካም የሪፎርም ቀን