የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በለውጡ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም 7 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ ዕድገት አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በለውጡ ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም 7 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ ዕድገት አስመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስድስት ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም 7 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ሪፎሩሙን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፏን ጠቅሰዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሺኝ፣ ግጭት፣ ድርቅ፣ የዓለም የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ ጫናዎችና ሌሎችም ተግዳሮቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሲፈትኑት መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህን ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 6 ዓመታት በአማካይ በ7 ነጥብ 1 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት 3ኛው ትልቁ ኢኮኖሚ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የኢኮኖሚ ባለቤት እንድትሆን አስችሏል ነው ያሉት።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በተሰጡ የፖሊሲ ድጋፎችና ኢንቨስትመንቶች የተገኘው ውጤት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ገልጸዋል።
በስንዴ ልማት ለዘመናት ከውጪ ይገባ የነበረን ምርት እንዲቀር ከማድረግ ባለፈ ስንዴን ወደ ውጪ በመላክ የገቢ አቅም ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
በሌላ በኩል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ተወዳዳሪነትና በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ሚና ከማሳድግ አንጻር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመጀመር እመርታ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥ ግጭትና በሌሎች ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ከ395 በላይ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተጀመረው ጥረት ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው።
ከቀላል ኢንዱስትሪዎች ባሻገር የኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ማምረቻ ዘርፎችም የሚያኮራ ውጤት እንደተመዘገበባቸው አንስተዋል።
ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለሀገራዊ ዕድገት በማዋል ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ አስችሏል ብለዋል።
ለአብነትም በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የቱሪዝም መዳረሻዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመገንባትና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማሻሻል ከፍተኛ ስራ መሰራቱን አመላክተዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ አዲስ አቅምን የፈጠረ ሲሆን ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንዲያደርጉ ለተጀመሩ ጥረቶች ወሳኝ አቅም ሆኗል ነው ያሉት።
አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ ለማድረግ በተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀከት የከተማዋን ውበትና ገጽታ በመቀየር አዲስ አበባን ተመራጭ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እያደረገ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ጨምረውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አራት ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል በወሳኝ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።
መንግስት የኢኮኖሚውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና ስር የሰደዱ ማነቆዎችን ለመፍታት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከነወነ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ኢኮኖሚውን ዘመናዊና ለውድድር ክፍት በማድረግ በግብርናው፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጂ ዘርፍ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።