የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች የሉዓላዊነት ጽኑ መሰረቶች - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች የሉዓላዊነት ጽኑ መሰረቶች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦በጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች የኢትዮጵያን የሉዓላዊ ክብር የሚያጸኑ መሰረቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ የዘመን መሸጋገሪያ የሆነችው አስራ ሶስተኛዋ የጳጉሜ ወር ቀናት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በተለያየ ስያሜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እየተከበሩ ይገኛሉ።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት "ጳጉሜ-1 የበጎ ፈቃድ፣ ጳጉሜ-2 የአምራችነት፣ ጳጉሜ-3 የሰላም፣ ጳጉሜ-4 የአገልጋይነት እና ጳጉሜ-5 የአንድነት ቀን" በሚል ስያሜዎች በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብረዋል።
ዘንድሮም የጳጉሜ ቀናት "ጳጉሜ-1 የመሻገር፣ ጳጉሜ-2 የሪፎርም፣ ጳጉሜ-3 የሉዓላዊነት፣ ጳጉሜ-4 የሕብር እና ጳጉሜ-5 የነገ ቀን" በሚሉ ስያሜዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያየ ዝግጅት በመከበር ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚገኘው የሪፎርም ቀን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም መስክ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች የተገኙ ውጤቶች የሚዳሰሱበት ለላቀ አገልግሎትም የቤት ስራ የሚወሰድበት ነው።
የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በዚህ ረገድ በአርአያነት የሚጠቀሱ ሲሆን ጠንካራ የሪፎርም ስራዎች ተከናወነውባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በጸጥታና ደኅንት ተቋማት የተወሰደው የለውጥ እርምጃ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚጸና የድል ሰራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ በዓል በተከበረበት ወቅትም የኢትዮጵያ ሠራዊት ሰላምን የሚጠብቅና የሚያጸና የህዝብ ልጅ ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥና በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮም የመፈጸም አቅሙን በብቃት በመወጣት ውድ ህይወቱን ከፍሎ የሰላም፣ የልማትና የአንድነት ምልክትነቱን አስጠብቆ የቀጠለ ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገር መካከለያ ሠራዊት የተካሄደው የሪፎርም እርምጃ በአስተሳሰብ፣ በአደረጃጀትና በማድረግ አቅም የአፍሪካ የሰላም ተምሳሌትና ምንጭ የሆነ ሠራዊት መገንባት አስችሏል ብለዋል።
በዚህም መከላከያ ሠራዊትን በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይልና በሳይበር ደኅንነት እንዲደራጅ በማድረግ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን በማሰናሰል የተሟላ ቁመና እንዲኖረው መደረጉን ገልጸዋል።
የተፈጠረው ጠንካራ አደረጃጀትም በተግባር የተፈተነ፤ ውጊያን ማድረግና መፈጸም የሚችል የድል ባለቤት የሆነ ሠራዊት የተገነባበት ስኬታማ የሪፎርም ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ መከላከያ ሠራዊት ዘመናትን ባስቆጠረ ተቋማዊ ግንባታ ሂደት ፈተናን በጽናት በማለፍ የሀገርን ህልውና ያስጠበቀ ኃይል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀግና አርበኞች ሀገር መሆኗ በጽናት ተፈትኖ ነጥሮ የወጣ፣ ጠንካራ ማንነትና ብቃትን የተላበሰ የማይበገር የመከላከያ ሠራዊት እንዲኖራት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በአየር ኃይል 88ኛ ዓመት ክብረ በዓል ወቅት በኢትዮጵያ የትጥቅ ዝግጁነትና ዘመናዊ ጦር የማቋቋም ስራ ከ116 ዓመታት በፊት መሰረት ተጥሎ በሂደትም ዛሬ ላይ በእጅጉ መዘመኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደደረገ በምድር ጦር፣ አየር ኃይል፣ በባህር ኃይል እና በሳይበር ደህንነት ትልቅ አቅም ያለው ዘመናዊ ተቋም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተካሄዱ የሪፎረም ተግባራት መከላከያ በአደረጃጀት፣ በሥነ-ልቦና እና በትጥቅ አቅም ትልቅ ዕምርታ እንዲያመጣ አቅም የፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ኢትዮጵያ ነሀሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፕላን ባለቤት መሆኗን አስታውሰዋል።
የአየር ኃይል ከ88 ዓመታት በፊት ተቋቁሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ኃይሎችን በመፋለም በተከፈለ ውድ መስዋትነት በርካታ ገድል ፈጽሞ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰ ተቋም ነው ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህም የአየር ኃይልን የዕድሜ አንጋፋነት መነሻ በማድረግ በሰው ሃይል፣ በትጥቅና በመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን የለውጥ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ ሀገራዊ ለውጡ ለሰላምና ደኅንነት ተቋማት ስኬታማ የለውጥ እርምጃ በር የከፈተ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በተወሰደ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ የሀገርንና የዜጎችን ብሔራዊ ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንዳስቻለ ገልጸዋል።
በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች አስተዳደሩ ኢትዮጵያን የራሷ የሰርቲፊኬት ቋትና የዲዛይን ሥርዓት የምታሳልጥበት ይፋዊ የቁልፍ የመሰረተ ልማት ሶፍትዌር ባለቤት እንድትሆን ያስቻላት መሆኑን ገልጸዋል።
ይፋዊ የቁልፍ የመሰረተ ልማት ሥርዓቱም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተቋቋመበትን የቁልፍ ተቋማትን ደኅንነት የማስጠበቅ ተልዕኮ የሚመግብ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ፤ ሀገራዊ ለውጡ በዜጎች የወንጀል ምርመራ ላይ ይፈጸም የነበረውን ሰቆቃ መነሻ በማድረግ ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወሰድ አንዱ ገፊ ምክንያት ነበር ብለዋል።
በዚህም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፍትሕና ጸጥታ ተቋማት ላይ ስኬታማ የለውጥ እርምጃ በመውሰድ በቴክኖሎጂ የዘመነ ስኬታማ ተቋማዊ ግንባታ መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት የለውጥ ዓመታትም ዜጎች ወንጀል ፈጽመው ሲገኙ ሕግና ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር የተከተለ የምርመራ ማካሄድ የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።