ለኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የዕውቅና የወርቅ ሜዳሊያ ተበረከተላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የዕውቅና የወርቅ ሜዳሊያ ተበረከተላቸው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2016(ኢዜአ)፦ የቻይና የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የዕውቅና የወርቅ ሜዳሊያ (Great Wall Commemorative Gold Medal Award) አበርክቷል፡፡
ለኮሚሽነር ጀነራሉ የተበረከተላቸው የወርቅ ሜዳሊያ የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት በማጠናከር በተለይም በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የፀጥታ ትብብር ስራዎች፣ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅትንና የቀጠናውን ትብብር ከቻይና ፖሊስ ጋር በማስተሳሰር ላበረከቱት ሚና መሆኑም ተገልጿል።
እንዲሁም እውቅናው አሁን ላይ የዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም የቦርድ አባል ሆነው ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተጫወቱ ላሉት ከፍተኛ አስተዋዕፆ የተሰጠ ሲሆን ፤በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የዕውቅና የወርቅ ሜዳሊያም ከቻይና የህዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዋንግ ዣዎሆንግ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱም ላይ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ፣ የቻይና የህዝብ ደኅንነት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሮች እና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ፡፡