ለወጣቶች የፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን የመሻገር ጉዞ ለማሳካት መሰረት የሚጥል ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች የፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን የመሻገር ጉዞ ለማሳካት መሰረት የሚጥል ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016 (ኢዜአ):- ለወጣቶች የፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን የብልፅግና እና የመሻገር ጉዞ ለማሳካት መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰመር ካምፕ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን ጎብኝተዋል።
በኤክስፖው በፈጠራ ስራ ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች ባለፉት አንድ ዓመት በሰመር ካምፕ ሆነው ያሻሻሏቸውን የቴክኖሎጂ ስራዎች አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተጀመረው የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የሰመር ካምፕ አቅም ማጎልበቻ የተሟላ ክህሎትና የፈጠራ እውቀትን የሰነቁ ወጣቶችን የሚያበራክት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወጣቶች በሁሉም መስክ ክህሎት የተላበሱ ሲሆኑ ራሳቸውንና ሀገራቸውን በመለወጥ ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን እንደሚችሉ አመላክተዋል።
የሀገር ዕድገት የሚረጋገጠው ከጀማሪ ስራ ፈጣሪነት በመነሳት በፍጥነት ከሚያድጉ ግለሰቦችና ቡድኖች መሆኑን አንስተው፥ በኢትዮጵያ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ ከባቢ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞው በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
በሰመር ካፕም ኤክስፖው የዘርፎችን ምርታማነት የሚያጎለብቱ፣ አገልግሎትን የሚያዘምኑና የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን የሚያስቀሩ ፈጠራዎች መቅረባቸው ለሀገር ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።
ሆኖም ቴክኖሎጂ መፍጠር ብቻውን ግብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ ጅምር ስራዎችን ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ወደ ሰፊ ምርት እንዲቀየሩ መስራት ይገባል፤ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የመበልፀግና ወደ ተሻለ ከፍታ የመሸጋገር ተስፋ ያላት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በሀገር ወዳድነት ሌት ተቀን መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወጣቶች በፈጠራ ሀሳቦቻቸው ምክንያት ከአመለካከት ጀምሮ በርካታ ጎታች ሁኔታዎችን ተቋቁመው ስኬት እንዳስመዘገቡት ሁሉ ኢትዮጵያም ፈተናዎችን ተቋቁማ ትሻገራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የመሻገር ጉዞ ማሳካት አትችሉም የሚል ዜና ግባችንን ከማሳካት አያቆመንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የልጆቿ ኩራትና የአፍሪካ የልማት ምሳሌ የሆነች ሀገርን ለመገንባት ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።