የባህል ህክምናን በጥናትና ምርምር በመደገፍ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 1/ 2016(ኢዜአ)፦የባህል ህክምናን በጥናትና ምርምር በመደገፍና ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማቀናጀት አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የአፍሪካ የባህል ህክምና ቀን "ጥራት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህል መድሃኒቶች አቅርቦትን በተገቢው የቁጥጥር ዘዴዎች በመደገፍ ማቅረብ" በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ረጋሳ ባይሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤በአገሪቱ ያለው የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ የባህል መድሃኒት ጥራቱና ደህንነቱ ተረጋግጦ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው።

በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በስልጠናና በልምድ ልውውጥ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

መድሃኒቶቹ ጥራታቸው፣ ደህነታቸውና ፈዋሽነታቸውን በማረጋገጥ ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ የሚያስችል መሆኑም እንዲሁ።

የባህል መድሃኒቶችን በጥናትና ምርምር በመደገፍና ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለባህል ህክምና አገልግሎት የሚውሉ እፅዋቶችን የመጠበቅና የማባዛት ስራ እየተካሔደ መሆኑንም አንስተዋል።

በ2016 ዓ.ም ከ1 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ የባህል መድሃኒቶችን በመመዝገብ ጥራታቸውንና ደህነታችውን የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የባህል ቀን እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ በመከበር ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ አብዛኛው ማህበረሰብ የባህል ህክምና ተጠቃሚ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የባህል መድሃኒት የማዘጋጀት ስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እውቅና ለመስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን አንስተዋል።

በዓሉ ላይ የጤና ሚኒስቴና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም