ቀጥታ፡

የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን

ጎንደር ፤ ጳጉሜን 1/2016 (ኢዜአ)፡- የተጀመሩ የልማት ፕሮጀቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ተናገሩት።

የ"መሻገር ቀን" ጳጉሜን -1 በከተማው በልማት ስራዎች ጉብኝትና በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት፤ በከተማው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀቶችን በማስቀጠል ለስኬት በመትጋት የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህልና ታሪክ ባለቤት መሆኗን ያወሱት አቶ ቻላቸው፤ ከለውጡ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ስኬት በየልማት ዘርፉ ማስመዝገብ መቻሉን አመልክተዋል።

እለቱን ስናስብ በከተማዋ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የሰላም ግንባታ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማለም ነው ብለዋል።

"የመሻገር ቀን" ቀን አዳዲስ ተስፋዎችና ውጥኖችን ይዘን ወደ አዲሱ ዓመት ለመሻገር መነሳሳት የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ መንግስቱ አስማረ ናቸው።


 

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሱሌማን ዳውድ በበኩላቸው፤ ዕለቱ ወደ ተሟላ ሰላምና ልማት ለመግባት ቃል የምንገባበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በእለቱም በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የዓጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥገና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክትና የኢንቨስትመንት ስራዎች ጉብኝት ተካሂዷል።

ቀኑን አስመልክቶ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይም በከተማው በግብርና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸው ተመላክቷክል።

በተካሄደው ጉብኝትና የፓናል ውይይት ላይም የከተማው አመራር አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም