ቀጥታ፡

ለብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ውጤታማነት ዜጎች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ትብብር ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፦ ለብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ውጤታማነት ዜጎች ትክክለኛ መረጃዎችን በመስጠት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የዜጎች የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ከመጪው መስከረም 1 ቀን 2017 ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት 600 ለሚጠጉ የብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ለአንድ ወራት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በዚሁ ወቅት፤ የሚካሄደው ጥናት የአገር ኢኮኖሚና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ያለበትን ደረጃ መሰረት በማድረግ የልማት ዕቅድና ፖሊሲን ለማመላከት ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡

ጥናቱ በርካታ አገራዊ መረጃዎችን የሚያካትት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ መረጃን መሰረት በማድረግ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ስራዎችን በፍጥነት ለማከናወን ትልቅ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

የጥናቱ ውጤታማ እንዲሆን የመንግስት መዋቅሮችን ጨምሮ ዜጎች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ መረጃ ሰብሳቢዎችም በቅንነት፣ በታማኝነትና በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ጥናቱ አገሪቱ በስራ ስምሪትና በስራ ዕድል ፈጠራ ለደረሰችበት ደረጃ ትክክለኛ መረጃን የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛ መረጃ የአገርን እድገትና የልማት ተልዕኮን ለማሳካት እንደሚያግዝ በመጥቀስ ጥናቱ ተካሂዶ ወደ ስራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ከመጪው መስከረም 1 ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት የሀገር ምጣኔ ሀብትና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ያለበትን ደረጃ ትክክለኛ መረጃን የሚያመላክት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጥናቱ የቤተሰብ ፍጆታ፣ የሰው ሃይል ስምሪት፣ የህዝብ ፍልሰትና የማህበራዊ ደህንነት አሰጣጥን በተመለከተ ሳይንሳዊ የሆነ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ ሲጠናቀቅም ለአምስት ዓመታት አገልግሎት እንደሚሰጥ በመጥቀስ ለሀገር አቀፍና ለዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ጥራት ያለው መረጃ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎቹ መካከል ሞሲሳ ማሞና ተክላይሁን ገዛኸኝ እንዳሉት ከስልጠናው ባገኙት እውቀትና ክህሎት መሰረት ጥራት ያለው መረጃ ለመሰብሰብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም