ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ ሀብቶችን ትውልዱ እንዲያውቃቸውና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ባህላዊ ሀብቶችን ትውልዱ እንዲያውቃቸውና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ አስታወቁ።

ቢሮው ለስድስተኛ ዙር የሚካሄደውንና መስከረም ወር ላይ ወጣቶች የሚጫወቱት ''ጎቤና ሺኖዬ'' የተሰኘውን የባህላዊ ጭፈራ ፌስቲቫል አስጀምሯል።

በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ እና ሌሎች የባህል ዘርፍ ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

''ጎቤና ሺኖዬ'' ወጣት ወንዶችና ሴቶች ክረምቱ አልፎ የ'ብራ' ወቅት መምጣቱን ለማመላከት በባህላዊ አልባሳት አጊጠው የሚጨፍሩት ባህላዊ ጭፈራ ነው።

ባህላዊ ጨዋታውና ጭፈራው ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ኢሬቻ ድረስ የሚካሄድ ሲሆን ወጣቶች ደስታቸውንና ተስፋቸውን የሚያንጸባርቁበት ባህላዊ ሁነት ነው።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ''ጎቤና ሺኖዬ''ን ጨምሮ የክልሉን ቱባ ባህል የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ባህላዊ እሴቶች ሳይደበዝዙና ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ አሁን ያለው ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ ሀብቶችን በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሲሆን እነዚህ ባህላዊ ሀብቶች የገቢ ምንጭ በመሆን ጭምር የክልሉን ኢኮኖሚ መደገፍ እንደሚያስችሉም ጠቁመዋል።

በመስከረም ወር እስከ ኢሬቻ ድረስ የሚጨፈረው ''ጎቤ እና ሺኖዬ'' ወጣቶች ጨፍረው ብቻ የሚለያዩበት ሳይሆን ባህሉን የሚያስተዋወቅበት ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ ሀብቶችን በትውልድ ዘንድ እንዲታወቁ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህዝቡ ቀደምት ባህላዊ እሴቶችን ህጋዊ መሰረት እንዲኖራቸው እያደረገ ጥቅም ላይ እያዋለ ሲሆን ከዚህም አንዱ የባህላዊ ፍርድ ቤት መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ''ቡሳ ጎኖፋ'' የተሰኘ የኦሮሞ ሕዝብ ችግር ሲያጋጥመው በራሱ አቅም ተረዳድቶ ችግሩን የሚያልፍበት መንገድም ተግባራዊ መደረጉን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም