አረንጓዴ አሻራ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ10 ዓመት ብዝሃ ሕይወት እቅድ ጋር ሊተሳሰር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ10 ዓመት ብዝሃ ሕይወት እቅድ ጋር ሊተሳሰር ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከተመድ የ10 ዓመት ብዝሃ ሕይወትን ዳግም ወደ ነባር ሕልውናው የመመለስ እቅድ ጋር የማስተሳሰር ፍላጎት እንዳለው የድርጅቱ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም አስታወቀ።
በኮትዲቭዋር ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
ልዩ ጉባኤው “ድርቅን በመቋቋም፤ የመሬት መራቆት እና በረሃማነት የመዋጋት ርምጃ የማፋጠን ጥረትን ማሳደግ” በሚል መሪ ሀሳብ ተከናውኗል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰንና ከተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (UNFCCC) ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የአየር ንብረትና የከባቢ አየር ፖሊሲዎች ቀርጻ በቁርጠኝነት እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የአየር ንብረትን ለውጥን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን እየተገበረ እንደሚገኝና እስከ አሁን ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን አመልክተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2015 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
አረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ስርዓትን ለመለወጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
የተመድ የተለያዩ ተቋማት የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥና ከባቢ አየር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማነት የሚያደርጉት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ያላትን መሪነት ተጠቅማ በሕዳር ወር 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን ባኩ በሚካሄደው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP29) የአፍሪካን ድምጽ አንድ ለማድረግ እየሰራች ነው ብለዋል።
የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ኢኒሺዬቲቮች ላይ እየወሰደች ያለው የአመራርነት ሚና አድንቀዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ አረንጓዴ አሻራ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የ10 ዓመት ብዝሃ ሕይወት ዳግም ወደ ሕልውናው የመመለስ እቅድ (UN Decade of Ecological Restoration) ጋር ለማጣጣምና ለማስተሳሰር ፍላጎት አለው ብለዋል።
ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ጋር በአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚፈልግም አመልክተዋል።
የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (UNFCCC) ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጠሚያ እቅዶች በመተግበር እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ዋና ፀሐፊው ኢትዮጵያ ለእቅዶቹ ተፈጻሚነት የሚያስፈልጋትን ሀብት ለማፈላለግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።