የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአንድ መቶ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአንድ መቶ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የአንድ መቶ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖና የባንኩ የሥራ አመራር አባላት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረገው ድጋፍ ማዕከሉ በ30 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ በአዲስ አበባ እያስገነባ ለሚገኘው የአረጋውያን ማረፊያና ሆስፒታል ህንጻ ግንባታ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
መቄዶንያ ምንም ገቢ ማመንጫ ሳይኖረው በለጋሾች ድጋፍ ብቻ የበርካቶች ሕይወት እንዲስተካከል፣ ከሕመም እንዲፈወሱና ከጉዳት እንዲያገግሙ እያደረገ ያለ የበጎ አድራጎት ማዕከል ነው።
መቄዶንያ ''ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው'' በሚለው መርህ አዲስ አበባ ጨምሮ በ33 የክልል ከተሞች ማዕከል በመክፈት ከ7 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች እገዛ እያደረገ ይገኛል።