የአገሪቱን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ በዘርፉ የባለተሰጥዖ ወጣቶችን ክህሎት ለማጎልበት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የአገሪቱን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ በዘርፉ የባለተሰጥዖ ወጣቶችን ክህሎት ለማጎልበት ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- የአገሪቱን የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ በዘርፉ የባለተሰጥዖ ወጣቶችን ክህሎት ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በድሮን ቴክኖሎጂ ንግድ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እውቅና ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አገራዊ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይንሳዊ ፈጠራ ክህሎት የበለጸገ ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በአከባቢ ጥበቅና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን የተጀመሩ ሽግግሮችን ስኬታማ ለማድረግ የባለተሰጥዖ ወጣቶችን ክህሎት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳንይስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያን ሽግግር በዘላቂነት ዕውን ለማድረግ አገራዊ የቴክኖሎጂ ዕድገት ማረጋገጥን ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንንም ተከትሎ በኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ የስፔስ ልጆች ክለብን በማቋቋም ተማሪዎችና ሌሎች አካላት የዘርፉን ጽንሰ ኃሳብ እንዲረዱና ከጽንሰ ኃሳቡም የፕሮጀክት ኃሳብ እንዲያፈልቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ጎን ለጎንም በመላ አገሪቱ የሚገኙ ባለተሰጥዖ ታዳጊ ልጆችን በዘርፉ የንግድ ሥራ ፈጠራ አፍላቂዎችን በመመልመል በክረምት መርኃ ግብር ሥልጠና በመስጠትና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም ለ4ኛ ጊዜ በክረምት መርኃ ግብር በአዲስ አበባ የሰለጠኑ ተማሪዎች መመረቃቸውን ገልጸዋል።
ከዛሬው ተመራቂዎች በተጨማሪም በተለያዩ ክልሎች በክረምት መርኃ ግብር ሥልጠና የተሠጠ መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ቀናት የሚመረቁ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ዛሬ እውቅና ከተሰጣቸው ሠልጣኞቹ መካከል በድሮን ቴክኖሎጂ ንግድ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ሠልጣኞች የራሳቸውን ድርጅት ማቋቋማቸውን ተናግረዋል።
ድርጅቶቹ ድሮን በመጠqም ሕንጻ ላይ የሚከሰት እሳት ማጥፋት፣ የህንጻ መስታወት ማፅዳትና ውሃን ወደ ሃይድሮጅን ነዳጅ የሚቀይሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኩባንያዎቹ እንዲቋቋሙ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።