የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በ2017 ዓ.ም ለ196 አዲስ ሰልጣኞች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በ2017 ዓ.ም ለ196 አዲስ ሰልጣኞች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠና ሊሰጥ ነው።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት 2005 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ በ2017 ዓ.ም ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ 196 ታዳጊዎችን ተቀብሎ በልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች እንደሚያሰለጥን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አምበሳው እንየው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ዘንድሮም አካዳሚው ከሐምሌ 25 ቀን እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ፤ አካዳሚውን የሚቀላቀሉ ታዳጊ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጀመሪያውን ዙር የእጩ ምልመላ ሲያካሄድ ቆይቷል።

አካዳሚው በዘርፉ በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸውን 128 መልማይ አባላት ከተለያዪ ተቋማት በመምረጥ እጩ ሰልጣኞችን የመምረጥ ሥራ እንዲሰሩ መደረጉን ተናግረዋል።


 

በእዚህም በመጀመሪያው ዙር የመረጣ መርሃ ግብር እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ 800 እጩ ሥልጣኝ ታዳጊዎችን መመልመላቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይ ከመስከረም 8 እስከ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአካዳሚው ለመሰልጠን ከተመዘገቡ 800 ሰልጣኞች መካከል 196ቱን የመምረጥ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ሰልጣኞችንም ለመለየት ከሚታዪ መስፈርቶች መካከል ታዳጊዎቹ እያንዳንዱ የስፖርት አይነት የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ምን ያህል አሟልተዋል የሚለውን መለየት፣ የጤና ሁኔታቸውና የሥነ ልቦና ዝግጁነታቸውን መፈተሽ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ታዳጊዎች ሰልጣኞች በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች ለአራት ዓመታት የሚቆይ ሥልጠና በአካዳሚው እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ከስፖርት አይነቶች ውስጥም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ ፣ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ እና ፓራሊምፒክ ተጠቃሽ መሆኑናቸውን ተናግረዋል።


 

ነገር ግን በ2017 ዓ.ም አካዳሚው በእግርኳስ የስፖርት አይነት ላይ ታዳጊዎችን ተቀብሎ የሚያሰለጥነው ሴቶችን ብቻ መሆኑን ገልፀው ይህም የሆነበት ምክንያት በአካዳሚው በቂ የወንድ እግርኳስ ሰልጣኞች በመኖራቸው መሆኑን አብራርተዋል።

ሙሉ ምልመላው ከተጠናቀቀ በኋላ አካዳሚው ባሉት የማሰልጠኛ ቦታዎች ከመስከረም 18 ጀምሮ አዲስና ነባር ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን እንደሚጀምር ገልፀዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የእጩ ሰልጣኞች ምልመላ ሳይካሄድ በቆየባቸው በአማራና ቤንሻንጉል ክልሎች ታዳጊ ስፖርተኞችን የመምረጥ ሥራ ለመሥራት ተቋሙ በዝግጅት ላይ መሆኑን አክለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ላይ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተሳትፎዋን ለማሳደግ ብቁ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት መንግሥት ብሎም የግሉ ዘርፍ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በ2017 ዓ.ም በልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች አጠቃላይ 750 የሚሆኑ አዲስና ነበር የስፖርት ሰልጣኞችን ተቀብሎ የሚያሰለጥን መሆኑን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም