እልፍ አእላፍ መከራዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተደራርበው ያላስቆሙትን የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ራዕይ ተሸክመን ዛሬ ላይ ደርሰናል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
እልፍ አእላፍ መከራዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተደራርበው ያላስቆሙትን የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ራዕይ ተሸክመን ዛሬ ላይ ደርሰናል - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፦እልፍ አእላፍ መከራዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተደራርበው ያላስቆሙትን የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ራዕይ ተሸክመን ዛሬ ላይ ደርሰናል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም የመሻገር ቀንን ምክንያት በማድረግ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፥ በደም የተከበረውን ሉዓላዊነታችንን በላብ ለማፅናት እያደረግነው ያለው ተጋድሎ በሕዝባችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ውጤታማነቱ ቀጥሎ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና በሚያሻግሩ ስኬቶች ታጅበን ዛሬ ላይ መቆም ችለናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሚያርፉባት የመከራ በትሮች ይበልጥ ፀንታ እንድትቆም አድርገዋት፣ ሕዝቦቿ በፈተና መሀል አንድነታቸውን እንደ አለት፣ ህብረታቸውን እንደ ብረት እያጠነከሩ አዲሱን የ2017 ዓመት ለመቀበል ከጫፍ ደርሰናል ነው ያሉት አቶ አደም በመልዕክታቸው።
ትናንት ያጋጠሙን ፈተናዎች የህዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ከማድረስ፣ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ከመሻገር፣ የስንዴ ፍላጎታችንን በሀገር ውስጥ በማሟላት ኤክስፖርት ማድረግ ከመጀመር፣ የአምራች ኢንዱስትሪ የተኪ ማምረት አቅም ከማጎልበት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከመገንባት፣ በአጠቃላይ እልፍ አእላፍ ስኬቶችን ከማስመዝገብ አላገዱንምና ክብሩን ፈጣሪ ይውሰድ ብለዋል።
በመጪው አዲስ ዓመትም ከትናንት ፈተናዎች ተምረን፣ የመሻገር ጥሪቶችን የአዲስ ብርሃን ወረቶች አድርገን፣ በአንደኛው የፓርቲያችን ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ቃል እንደገባነው ከፈተና ወደ ልዕልና መሻገራችንን እና ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ብልፅግና ማሻገራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።