በብሔረሰብ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሻጋሪ ስራዎቸ ይከናወናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሻጋሪ ስራዎቸ ይከናወናሉ
ሰቆጣ ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአዲሱ በጀት ዓመት የተፈጥሮ ሀብትን በማልማትና የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት አሻጋሪ ተግባራት እንደሚከናወኑ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጳጉሜን 1 ''የመሻገር ቀን'' በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ እንደገለፁት፤ ''የመሻገር ቀን'' ሲከበር በብሔረሰብ አስተዳደሩ በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል የሚከናወኑ ተግባራትን በማጠናከር ሊሆን ይገባል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ያለውን ሃብት አልምቶ በመጠቀም በምግብ ራስን ለመቻል ከምንጊዜውም በላይ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንዲሁም የተሻሻሉ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን ገቢራዊ በማድረግ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ጎልብቶ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችን በመስኖ ለማልማት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ ሃይሉ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ማስፋትም በአዲሱ ዓመት የትኩረት መስክ ነው ብለዋል።
የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው፤ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ120 ሺህ ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ይገኛል ብለዋል።
ይህንን የመሬት ሃብተ በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችና የአሰራር ስልቶች በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን በዘላቂነት ለመላቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለዚህ ስኬታማነትም ለአካባቢው አየር ፀባይና መልክዓ ምድር ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ስራ ከሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ከሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት ጋር በመተባበር 20 ሺህ እናቶችን በጓሮ አትክልት፣ በዶሮና ፍየል እርባታ ሥራ ላይ ማሰማራት መቻሉን ገልፀዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ የውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን አብርሃም አሰፋ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 375 የውሃ ተቋማትን በመጠገን የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
አካባቢን ከተፈጥሮ ደን መመናመን ለመታደግ የባዮ ጋዝና የሶላር ኢነርጂ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በብሄረሰብ አስተዳደሩ ጳጉሜን 1 ''የመሻገር ቀን'' የአመራር አካላትና ባለሙያዎች በተገኙበት በሰቆጣ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የጳጉሜን-1 "የመሻገር ቀን" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ኢትዮጵያ መሻገሯ የሚታይበት ዕለት ሆኖ እንደሚከበር የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።