ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለመሻገር የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ - ኢዜአ አማርኛ
ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለመሻገር የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ
ድሬዳዋ፤ ጳጉሜ 1/13/2016 (ኢዜአ) :- ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመረዳትና በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለመሻገር የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ አስታወቁ።
የጳጉሜን-1 "የመሻገር ቀን" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቷ እየተከበረ ይገኛል።
ቀኑ በለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ኢትዮጵያ መሻገሯ የሚታይበት ዕለት ሆኖ የሚከበር ነው።
የድሬዳዋ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት አመት የላቀ የስራ አፈፃፀም ላሳዩ ተቋማትና ፈፃሚዎች ዕውቅና በመስጠት ቀኑን በማክበር ላይ ይገኛል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በነበሩት ዓመታት በከተማው በሁሉም ዘርፎች ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በድሬዳዋ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት፣ በሌማት ትሩፋት ፣ ግብርና ፣ ትምህርትና ጤና ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል ።
በድሬዳዋ በተቀናጀ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ነፃ የንግድ ቀጠናና የደረቅ ወደብ ተርሚናል ለአገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
በተከናወኑት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ድሬዳዋን የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ከማረጋገጥ ባሻገር በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች ኑሮ መለወጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
ያሉንን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ወደ ላቀ ደረጃ ለመሻገር የተቀናጀ ጥረት እናደርጋለን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ።
የዛሬው የመሻገር ቀንም በራሳችን ሃብቶችና ፀጋዎች የመጠቀምና የመኩራት ባህልን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ከማድረግ አኳያ ጥሩ መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
"የመሻገር ጥሪቶች፣ የአዲስ ዘመን ወረቶች" በሚል ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘው የመሻገር ቀን ላይ በድሬዳዋ በተጠናቀቀው በጀት አመት በየዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ፈፃሚዎች ዕውቅና ተሰጥቷል።
በሚዲያው ዘርፍ ዕውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከልም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተጠቃሽ ነው።
ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን የመሻገር ቀን ምክንያት በማድረግ የአስተዳደሩ አመራሮች የአምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ እንቅስቃሴዎች እንደሚጎበኙ ተመላክቷል።