የተገኙ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
የተገኙ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግተን እንሰራለን ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
‘‘የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች’’ በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜ 1- የመሻገር ቀን በፓናል ውይይትና ሌሎች ዝግጅቶች በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉ ህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ መልካም የልማት ጅምሮችን አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ሀገር የግብርና ልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከተረጅነት ለመላቀቅ የታለመውን ግብ ለማሳካት ተግተን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።
የመሻገር ቀን በዓል ሲከበር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜውን ባገኘበትና ተጨማሪ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት በጀመሩበት ጊዜ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ ባላፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ተግባራትን አስመልክቶ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ባዘጋጀው በዚሁ የፓናል ውይይት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን የግብርና ልማት ውጤቶች አውደ ርዕይ ምልከታም ተካሄዷል።
የጳጉሜን-1 "የመሻገር ቀን" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ኢትዮጵያ መሻገሯ የሚታይበት ዕለት ሆኖ እንደሚከበር የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።