በሐዋላ ገንዘብ ለሚልኩ ዜጎች የቤት መሥሪያን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት የሚውል 100 ቢሊየን ብር ብድር ተዘጋጅቷል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በሐዋላ ገንዘብ ለሚልኩ ዜጎች የቤት መሥሪያን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት የሚውል 100 ቢሊየን ብር ብድር ተዘጋጅቷል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ባንኮች በሐዋላ ገንዘብ ለሚያስተላልፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቤት መሥሪያን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት የሚውል 100 ቢሊየን ብር ብድር ማዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።
ባንኩ የውጭ ምንዛሬ የሐዋላ (remittance) ቢሮ ለሚከፍቱም ከሁለት ሳምንት በኋላ ፈቃድ መስጠት እንደሚጀመርም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ደቦ" በሚል ሥያሜ የተዘጋጀውን የውጭ የሐዋላ ፍሰት የሚያስተዋውቅበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ትላንት አካሂዷል።
በዚህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ለ6 ወራት የሚቆይ ንቅናቄ ተጀምሯል።
የሐዋላ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ዜጎች (unite.et) የተሰኘ የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ መክፈትና ገንዘብ ማስተላለፍ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።
የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ በመክፈት ተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባና በጊዜ የተገደበ የውጭ ምንዛሬ አማራጭ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ አገራት ዜጎች የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ በመክፈት አገልግሎቱን መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያ በትይዩ ገበያና በባንኮች መካከል የነበረው ከፍተኛ ልዩነት መልክ እንዲይዝ አስችሏል ብለዋል።
የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ የሐዋላ (remittance) አገልግሎት የማቋቋሚያ ፈቃድ መቀበል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚህም ፍላጎት ያላቸው አካላት የተዘጋጀውን መልካም ዕድል መጠቀም እንደሚችሉ ጥሪ አቅርበው፤ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ማመልከቻ ቅበላ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሥርዓቱ ከሕገ-ወጥ አሰራር በጸዳ መልኩ የሐዋላ መቀበያ፣ ማስተላለፊያና መጠቀሚያ ሥልቶችን ምቹና ቀልጣፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ደንበኞችን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአካል ብቻ ሳይሆን ባሉበት ሆነው (unite.et) በተሰኘው የዲጂታል መተግበሪያ የሐዋላ አገልግሎት መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ለዚህም በባንኮች አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ የሐዋላ (remittance) ገንዘብ ለሚልኩ ዜጎች የተሻለ የማበረታቻ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች በሐዋላ ገንዘብ ለሚያስተላልፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የቤት መሥሪያን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት የሚውል 100 ቢሊየን ብር ብድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጡ አሰራሮችን የሚጥሱ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።