የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሻገር ዘመን ማብሰሪያ ነው - ኢንጂነር አሸብር ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሻገር ዘመን ማብሰሪያ ነው - ኢንጂነር አሸብር ባልቻ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁማ ለስኬት ያበቃችው የሕዳሴው ግድብ የመሻገር ዘመን ማብሰሪያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን "የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ኃሳብ እየተከበረ ይገኛል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ እንደ ሀገር ፈተናዎችን ተቋቁሞ ወደ ስኬት ማማ መውጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዳሉት፣ የሕዳሴው ግድብ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተወሰደ ፈጣን የማሻሻያ ርምጃ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ከለውጡ በፊት ግድቡ በውድቀት አፋፍ ላይ እንደነበር ገልጸው፣ በግድቡ ላይ በተሰራው የማሻሻያ ሥራ አሁን ላይ ግድቡ ከአንድ ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ ከመፈፀም ውጭ ምንም ሚና እንዳልነበረው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የፕሮጀክት አስተዳደር ለውጥ በማድረግ ግድቡን የማዳን ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ሂደት ወደ መስመር ሲገባ ከፍተኛ ጫና እንደደረሰበት ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን እነዚህን ፈተናዎች በአንድነት በመሻገር ያስመዘገቡት ብሔራዊ ስኬት መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በጋራ በማሰለፍ ወደ ብልፅግና ማማ የወጡበት የታሪክ እጥፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሕዳሴው ግድብ የመሻገር ዘመን ማብሰሪያ ነው ሲሉም ነው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የገለጹት።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘቡን እውቀቱንና ጉልበቱን ያፈሰሰበት አንጡራ ኃብት መሆኑን ጠቅሰው የግድቡ ስኬት በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ መድገም እንደሚገባ ተናግረዋል።