ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበት የስኬት ደረጃ ከድኅነት ወደ ብልፅግና የመሻገር ተምሳሌት ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበት የስኬት ደረጃ ከድኅነት ወደ ብልፅግና የመሻገር ተምሳሌት ነው ሲሉ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

የዘንድሮው ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን በሚል ሥያሜ "የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ኃሳብ እየተከበረ ይገኛል።

ሥያሜውም የለውጡ መንግሥት የሀገር እድገትና አብሮነት መሰረት የሆኑት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና አምራች ኢንዱስትሪዎች ከነበሩበት ማነቆ ወጥተው ኢኮኖሚውን በእጅጉ ማንቀሳቀስ በመጀመራቸው የተሰጠ ነው።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት መልስ ያገኙበት ነበር።


 

ይሁንና በግድቡ ግንባታ ሂደት ያጋጠመው የፕሮጀክት አመራር ቀውስ ግድቡ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ከለውጡ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥናት ላይ የተመሰረተ ፈጣን የፕሮጀክት አስተዳደር ለውጥ በማድረጋቸው ግድቡን ከውድቀት መታደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ግድቡ አሁን ላይ የመገባደጃ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከድኅነት ወደ ብልፅግና፣ ከጨለማ ወደ ብርሀን የተሸጋገሩበት ሜጋ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።

የሕዳሴው ግድብ ከኃይል ልማት ባሻገር ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ በመፍጠር ወደ ዘርፈ ብዙ ስኬት የሚያሻግር መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲሱን 2017 ዓ.ም ስንቀበል በታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች ታጅበን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የጉባን ሀሩር ወደ ጸጋና በረከት የሚቀይር ድል መመዝገቡን አስታውሰዋል።

በህዳሴው ግድብ ላይ ለተመዘገበው ሀገራዊ ስኬት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሚናቸው የጎላ እንደነበርም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም