ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት መሻገርን የሚያመላክቱ ናቸው - አቶ መላኩ አለበል

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 01/2016 (ኢዜአ)፡-የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት መሻገርን የሚያመላክቱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለውን የጳጉሜን 1 "የመሻገር ቀን"ን አስመልክቶ "ከዘመን ወደ ዘመን በተስፋ እንደምንሻገር ሁሉ ከድህነት ወደ ብልጽግና እንሻገራለን" በሚል መርህ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፓናል ውይይት አካሂዷል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ውይይቱን በመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ወዲህ በተለይም ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሥራዎች ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ውጤቶች መሻገርን የሚያመላክቱ ናቸው።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃና እንዲያድግ ለማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣የገቢ ምርትን በመተካት፣ የወጪ ምርትን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድልን በማስፋፋት ጨምሮ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ አስቻይ ሁኔታዎች እንደነበሩ የገለፁት አቶ መላኩ፤ "የሕግ ማዕቀፎች አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ እንዲሆኑ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልና ሌሎች ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ሥራዎች ሰርተናል" ብለዋል።

ለአብነት ከዚህ በፊት በባንኮች ከሚቀርበው ብድር ውስጥ 70 በመቶው ለመንግስት 30 በመቶው ደግሞ ለግሉ ዘርፍ ሲቀርብ መቆየቱን ጠቅሰው፤ "በአሁን ወቅት 80 በመቶው ለግሉ ዘርፍ ቀሪው 20 በመቶው ለመንግስት ብድር እንዲቀርብ እየተደረገ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሚያደርገው ትኩረትና ሁለንተናዊ ድጋፍ በመጪዎችም ዓመታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የ10 ዓመት ግቦች መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

በ10 ዓመት ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ድርሻ ከሰባት በመቶ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ፤ የማምረት አቅም አጠቃቀምን ከ59 በመቶ ወደ 85 በመቶ የማሳደግ ግብ መኖሩን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የገበያ ድርሻን ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ፤ 500 ሚሊዮን ዶላር የማይበልጠውን የወጪ ንግድ ድርሻ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፤ "የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከዓመት ወደ ዓመት እመርታዎችን እያሳየ በለውጥ ውስጥ እየቀጠለ ነው" ብለዋል።

ለአብነት በ2016 በጀት ዓመት የዘርፉ አጠቃላይ ዕድገት 10 በመቶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ታረቀኝ፤ "ተኪ ምርቶች ላይ ከወጪ ንግድ እኩል ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ከውጭ ይመጣ የነበረ ምርት መተካት ችለናል" ብለዋል።

አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እንዲሁም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፉ በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው፤ በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በክልሎች ያለውን ኢንዱስትሪ በማነቃቃት ረገድ ውጤት እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

"በዚህም ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እርሾ በመሆንና የግብዓት ሰንሰለት በመፍጠር እንዲሁም ሰፊ የሰው ኃይል ወደ ሥራ በማስገባት ጉልህ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ትኩረት አድርገንባቸው እየሰራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህም በዘርፉ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንና ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት በተኪ ምርትና በወጪ ንግድ ግዙፍ ለውጥ እንደምታመጣ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ሀብታሙ ስማቸው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በኮሮና ወረርሽኝ ብሎም በሌሎች አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖዎች የበርካታ አገሮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዕድገት ሲቀንስ በኢትዮጵያ ግን ማደግ ባለበት መጠን ባይሆንም እድገት አሳይቷል።

"ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ስህበት ማጠንጠኛ አምራች ኢንዱስትሪው በመሆኑ በዚሁ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የመጣ ውጤት ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ከ4 ሺህ 600 በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መኖሩን ጠቁመው፤ በአብዛኛው በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አምራች ዘርፉ የአገሪቷን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስህበት ዘላቂ እንዲሆን የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

"በ2016 በጀት ዓመት ባጠቃላይ ለ329 አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጥተናል" ያሉት አማካሪው፤ 246 የሚሆኑት በአምራች ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ አገር የተፈጠሩ አስቻይ ሁኔታዎችና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ዘርፉ በቀጣይም እድገቱ እንደተጠበቀ እንዲቀጥል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

የጳጉሜን-1 "የመሻገር ቀን" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ኢትዮጵያ መሻገሯ የሚታይበት ዕለት ሆኖ እንደሚከበር የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም