የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከተማዋን ለመለወጥ አስገራሚ ስራ ሰርተዋል- የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከተማዋን ለመለወጥ አስገራሚ ስራ ሰርተዋል- የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016 ዓ.ም (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ አስገራሚ ስራ ሰርተዋል ሲሉ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ተሳታፊዎች ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ መከናወን ጀምሯል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፎረሙ ታዳሚዎች አዲስ አበባ ዓለምአቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።
ከተማዋ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥንና ለነዋሪዎቿ የሚመች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎቶችን እያዘመነች መሆኗንም ነው ያነሱት።
የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የከተማዋን አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸው የዜጎችን ኑሮ ከመቀየር ባለፈ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት።
ከጋና የመጡት የፎረሙ ተሳታፊ ጆን ዱብዌ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የልማት ፋይናንስን በማፈላለግ ከተሞችን ማዘመን ላይ ውስንነት አለባቸው ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባን ለማዘመን እየሰራች ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የስዋቲኒ ቤቶች ልማት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ዱአሚኒ እንደሚሉት በከተማዋ በአጭር ጊዜ የተከናወኑ ስራዎች ብዙ ነገር የሚያስተምሩ ናቸው።
ቁርጠኝነቱና ተነሳሽነቱ ካለ ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል አዲስ አበባ ትልቅ ማሳያ መሆኗንም አመልክተዋል።
ከግብጽ ማንሱራ ዩኒቨርስቲ የምህንድስና መምህሯ ኤያን አብዲ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን የመመልከት ዕድል ማግኘታቸውን ነው ያነሱት።
የከተማዋ ለውጥ ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥና መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የከተሞች ልማት ክፍል ሃላፊ ስቴቨን አቺያ ከተማዋን የሚያውቋት ከአስር ዓመታት በፊት እንደነበር ነው ያስታወሱት ።
የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ስራዎች በአጭር ጊዜ መከናወናቸው እንዳስገረማቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከተማዋ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንደምትሆን አንስተዋል።
ከስዋቲኒ የመጡት ሌላዋ የፎረሙ ተሳታፊ ሉንጂል ዲላሚኒ ከተማዋን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።
የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ የአገራቸውን ከተሞች የማዘመን ስራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።