በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የመሻገር ምልክት ነው -ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የመሻገር ምልክት ነው -ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016(ኢዜአ)፦ በግብርናው መስክ በስንዴ ምርታማነት የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የመሻገር ምልክት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን "የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል።
የኢትዮጵያን መሻገር ከሚያመላክቱ ነገሮች ውስጥ አንዱ ግብርና ሲሆን ከዚህም ውስጥ ስንዴ አንበሳውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተያዘው የመኸር ወቅት ብቻ ከ4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ መታረሱን ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ግብርና ወደ ዘመናዊ እርሻ እየተሻገረ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ስንዴ በዝናብ ወቅት ብቻ ሲመረት እንደነበር አስታውሰው፤ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን በመስኖ በመዝራት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ከመቻል አልፋ ባለፈው ዓመት ወደ ውጪ በመላክ ታሪክ ፈጽማለች ይህም አገሪቱ ወደ ብልጽግና የምታደርግውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው ብለዋል።
ስንዴን በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ሽግግር መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት በዝናብ የሚለማው ስንዴ 1 ነጥብ 75 ሚሊየን ሄከታር እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ከ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ይህም ምርትና ምርታማነቱ ከእጥፍ በላይ በመጨመር በአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን 27 ኩንታል ምርት አሁን በአማካይ 37 ኩንታል መድረሱን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ የኩታ ገጠም እርሻ፣ የተሟላ የግብዓት አቅርቦትና የመካናይዝድ እርሻ በስንዴ ልማቱ ላይ በተሳካ ሁኔታ መተግበር መቻሉን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ መንገድ ጀምራለች ያሉት ሚኒስትሩ አንዳንድ ቦታዎች በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ አሁን ላይ ከራሱ አልፎ የግብርናውን ሽግግር ለማሳለጥ ለወጪ፣ ለተኪና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት እያመረተ ይገኛል ብለዋል።
በአገሪቱ 20 በመቶ የሚጠጋው የእርሻ ስራ በሜካናይዜሽን እየታረሰ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ግብርናውን ከበሬ ትከሻ ለማላቀቅ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ዘዴ መታረሱን ጠቅሰው በ2016/17 ምርት ዘመን ምጣኔውን ወደ 12 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ስንዴ ላይ የተገኘውን ውጤት ወደ ሌሎች ምርቶች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በ2016/17 ምርት ዘመን መኸር እርሻ 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 614 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።