ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዛ እየሰራች እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
በኢትዮጵያ የሚመራው 10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ ዛሬ በኮትቭዋር አቢጃን መካሄድ ጀምሯል።
ልዩ ጉባኤው “Raising Ambition for Accelerating Action on Drought Resilience and Combating Land Degradation and Desertification” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር የመሬት መራቆት፣ የበረሃማነት መስፋፋትና ድርቅ የአፍሪካ ቁልፍ የልማትና የደህንነት ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም ችግሮች ምንጭና አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የመሬት መራቆት፣ የበረሃማነት መስፋፋትና ድርቅ መቋቋሚያ ተጨባጭ እርምጃዎችን በቁርጠኝነት እየወሰደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2015 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው በማሳያነት የጠቀሱት።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ችግኝ መተከሉንና ነሐሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።
የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስተባበር የተከናወነው ተግባር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየወሰደች ላለው ተጨባጭ እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያን እድገት የሚያፋጥኑ የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች እየወሰደች መሆኗንም ገልጸዋል።
የምግብና የስርዓተ ምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጫ ፕሮግራሞች፣ የከተሞች ዘላቂ ልማትና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማበረታቻ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች እንደሚጠቀሱና ሌሎች አገራትም ተሞክሮ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ መሪነት ከተቀበለችበት ነሐሴ 2015 ዓ.ም አንስቶ በርካታ የጉባኤውን ውሳኔዎች እንዲተገበሩ በማድረግ ከፍተኛ የመሪነት ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የአካባቢ መድረኮች በአንድ ድምጽ መወከል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የአፍሪካ ሀገራትን በአካባቢ ልማት የሚያስተሳስሩ የፖሊሲ እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለነዚህ ተግባራት ስኬታማነት አበክራ እንደምትሰራም በመግለጽ።
ጉባኤው እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ ውሳኔዎችና የጋራ አቋሞችን ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።