በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ተወካዮች ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የከተሞች ፎረም "ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ ከአፍሪካ ከተሞች የተውጣጡ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተወካዩች ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ እየተለዋወጡ ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የዘርፉ ተወካዩች፣ አጀንዳ 2063 በከተሞች ልማትና አጠቃላይ እድገት በመታገዝ የምንመኛትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ለዚሁ ማሳያ ደግሞ ኢትዮጵያ በተለይ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በራስ አቅም ፣ ፓርኮችን፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባቷን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካን በመወከል በፎረሙ እየተሳተፈ ያለው ኮላኒ ማሳኒ ኢትዮጵያ በርግጥም በከተማ ልማት የሚደነቅ ስራ እየሰራች ነው ሲል ተናግሯል።
በዚህም አዲስ አበባ በአፍሪካ በፈጣን የከተማ እድገትና ልማት በተምሳሌትነት የምትጠቀስ መሆን መቻሏን ነው የተናገረው።
ከናይጄሪያ የመጡት የፎረሙ ተሳታፊ አማኡ ያና በበኩላቸው፣ ከአስር አመታት በፊት አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን በማስታወስ አሁን ያዩት የከተማዋ እድገት እጅግ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የታየው አስደናቂ የከተማ ልማት ያላሰለሰ ጥረት ውጤት መሆኑን በማንሳት አፍሪካ ይህን ማሳካት እንደምትችል ማሳያ ነው ብለዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የዩኤን ሀቢታት የፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ተወካይ ሬሚ ሲጄፒ በበኩላቸው በተለይ በአዲስ አበባ ከታዩት የልማት ስራዎች ለህዝብ የመዝናኛ ስፍራዎች የተሰጠው ትኩረት ቀልብ የሚስብ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የአፍሪካ ከተሞች አረንጓዴና ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል የአዲስ አበባን ተሞክሮ ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል።
ዘላቂ የከተሞች እድገት እንዲፋጠን የአፍሪካ መንግስታት ስትራቴጂ በመንደፍ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አክለዋል።
እንዲሁም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በአህጉሪቷ ለዘላቂ የከተሞች ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ ሊጨምሩ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቅሰዋል።