ግብርን በታማኝነት መክፈል ለሀገር ዕድገትና ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የሚያኮራ የዜግነት ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ግብርን በታማኝነት መክፈል ለሀገር ዕድገትና ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የሚያኮራ የዜግነት ተግባር ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በገቢዎች ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከግብር ከፋዮች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ሀገራዊ ግብን ለማሳካት ግብርን በታማኝነትና በፈቃደኝነት መክፈል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር በዚሁ ወቅት፤ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን ለመሰብሰብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የሚሰበሰበውን የገቢ መጠን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በተያዘው በጀት ዓመት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን በአንድ በመቶ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከግብር የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚከፈልን ግብርን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተሰሩ የሚገኙ የለውጥ ስራዎች ለግብር ከፋዩ የአገልግሎት አሰጣጥ መሳለጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ግብር ከፋዩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ካለበት ሆኖ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣም አሰራሮች መዘርጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከግብር ማሳወቅ እስከ መክፈል ያሉ ሂደቶች በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እንዲያከናወኑ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በገቢዎች ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኪሮስ ደበሱ እንዳሉትም፤ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ታክስ በብቃት ለመሰብሰብ ከግብር ከፋዩ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ግብርን በታቀደው መሠረት ለመሰብሰብም ግብር ከፋዩ በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡
ግብርን በታማኝነት መክፈል ለሀገር ዕድገትና ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የሚያኮራ የዜግነት ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ ግብር ከፋዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ግብራቸውን በታማኝነትና በፈቃደኝነት በመክፈል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ግብርን በታማኝነት መክፈል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ግብራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች ተጠቅመው መክፍል መጀመራቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህም ጊዜያቸውን ከመቆጠብ አንጻር ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡