ባለሃብቶች በመንግስት እየተከናወነ ያለውን ምቹ የፖሊሲ ምህዳር በመጠቀም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቶች በመንግስት እየተከናወነ ያለውን ምቹ የፖሊሲ ምህዳር በመጠቀም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ባለሃብቶች በመንግስት እየተከናወነ ያለውን ምቹ የፖሊሲ ምህዳር በመጠቀም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ጥሪ አቀረቡ።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር)፣ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መድረኩ በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ አዳዲስ እድሎችና በባለሀብቶችና በቁልፍ ባለድርሻ አካላት መካከል ቀጥተኛ ተሳትፎና ትብብር መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከተደረጉ ማሻሻያዎች የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ሚና ያለውን የሎጅስቲክ አገልግሎት የላቀ ለማድረግ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችሉ ቁልፍ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አክለዋል።
የፋይናንስ አቅርቦት ስርዓቱን ምቹ ከማድረግ አኳያ በብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ ተደርጓል ነው ያሉት።
የኃይል አቅቦትን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ በትኩረት መሰራቱንም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ የተደረጉ ድጋፎች፤ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ የማኑፋክቸሪንግ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረው ይህም ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻሉን ነው የጠቀሱት።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው እያለሙ የሚገኙና፣ ለማልማት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አስገዝበዋል።
የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው መንግስት የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ከባለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ የለውጥ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዚህ ማሳያ መሆኑን ተናግረው ይህም ዘርፉን ለማሳደግ አይተኬ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ አገር የምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲተመን መደረጉ በርካታ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፉ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል።
ባለሃብቶችም ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በዘርፉ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ፓርኮቹ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በተኪ ምርት ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እየተወጡ እንደሚገኙ በመጥቀስ ከዚህ በመነሳት ፓርኮቹን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ለመቀየር የህግ ማዕቀፍ ተጠናቆ ወደ ስራ እየተገባ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መቀየር በንግድ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሎጂስቲክስ ዘርፍ በመታገዝ የከተማ ልማት ማዕከል ያደርጋቸዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዳሉ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ናቸው።
ኮሚሽኑም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።