ኢትዮጵያ ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ የተከተለችው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የፋይናንስ አማራጭ ውጤታማ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ የተከተለችው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የፋይናንስ አማራጭ ውጤታማ ሆኗል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ የተከተለችው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የፋይናንስ አማራጭ ስኬታማ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ላይ የዛሬ ውሎ በከተማ ልማት ፋይናንስ አማራጭ ላይ ያተኮረ ፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት የአፍሪካ የክትመት ምጣኔና የኢኮኖሚ ድርሻ በፍጥነት እየተለወጠ ነው።
የኢትዮጵያ ከተሞች በራሳቸው ያልተማከለ አስተዳደር አቅማቸውን እንዲገነቡ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም በግብር አሰባሰብና ልዩ ልዩ የፋይናንስ ምንጭ አማራጮችን በማስፋት ከተሞች ራሳቸውን እንዲያለሙ የተደረገው ጥረት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ነው ያነሱት።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከተሞች በፋይናንስ እየጎለበቱና ለኑሮ አመቺ በሆነ አግባብ በፍጥነት እያደጉ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በአዲስ አበባ ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ እየተካሄደ ያለው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የፋይናንስ ምንጭ አማራጭ ውጤት ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሮች በየደረጃው ያላቸውን የገቢ አማራጭ እንዲያሳድጉ ከማድረግ አኳያ በአዲስ አበባ የንብረት ግብርን ለአብነት ጠቅሰው፣ ይህ የፋይናንስ ጉድለትን ለማሟላት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የተቀናጀ አጋርነት ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ አማራጭ ውጤት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህም ተግዳሮትን የሚቋቋም ክትመት ለማረጋገጥ የከተሞችን ያልተማከለ አስተዳደር ማጠናከር፣ የሰው ሃይልና ተቋማዊ አቅም መገንባት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ ግብር ከመክፈል ባሻገር ዘላቂ ከተማ ልማት ላይ ያላቸውን አጋርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።