በደሴ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር ሰላምን ለማጽናት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር ሰላምን ለማጽናት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ
ደሴ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ አስተዳደር የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተግባር ሰላምን ለማጽናት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የወንጀል መከላከል ተግባራት መጠናከር በሚቻልባት ዙሪያ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ወቅት የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበባው አሻግሬ እንዳሉት፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚፈፀሙ ወንጅሎችን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት አምጥቷል።
ይህም በከተማው ሰላምን በማጽናት የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራውን በማጠናከር የከተማውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ አባላት ጎን በመሆን ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጠል አመልክተዋል።
በደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ የአረብ ገንዳ ሰፈር ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ኦፊሰር ሳጅን ስንሻው ጋሹ ፤ ከህብረተሰቡ ጋር የጀመርነው የወንጀል መከላከል ስራ ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
በዚህም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና በማንቃት በሌሊት ጭምር ተደራጅቶ አካባቢውን ከመጠበቅ ባለፈ ለፀጥታ አባላት መረጃና ጥቆማ እንዲሰጥ በመደረጉ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
መጪዎቹ በዓላት በሰላም እንዲከበሩና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከህዝብ ጋር ተቀናጅተው መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት መስፍን ተፈራ በማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ተደራጅተው ሌሊት ጭምር አካባቢያቸውን እየተጠበቁ መሆኑን ጠቁሞ፤ በዚህም ህብረተሰቡ ያለ ስጋት ወጥቶ መግባት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲል ገልጿል።
ከሰሞኑ መናሃሪያ አካባቢ መንገደኞችን አታለው 70 ሺህ ብርና የእጅ ስልክ ሰርቀው ለመሰወር የሞከሩ ግለሰቦችን ተከታትለው በመያዝ ንብረታቸውን ከማስመለስ ባለፈ ወንጀለኞችን ለህግ እንዲቀርቡ ማድረጋቸውንም ጠቅሷል።
ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ፀሐይ መሀመድ፤ በተፈጠረላቸው አደረጃጀት አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ ሰላማቸውን እያስከበሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስርቆትና ዝርፊያን በመቀነስ የተሻለ ሰላም ማስፈን እንደተቻለም አመልክተዋል።
በመድረኩ የከተማው አመራርና የፀጥታ አባላት፣ የከተማው ነዋሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።