የኢሬቻ በዓል ለማክበር የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል ለማክበር የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ በመስከረም 2017 ዓ.ም በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የሚታደሙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ ወደ አገራቸው መጥተው የኢሬቻ በዓልን በጋራ እንዲያሳልፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይሄንኑ መነሻ በማድረግ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬትና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሚን ጁንዲ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኢሬቻ በዓል ላይ በመታደም ከአገሩ ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጠናክር ፕሬዚዳንት ሽመልስ ጥሪ ማቅረባቸውን አንስተዋል።
ጥሪ ከተደረገ በኋላ የክልሉ መንግስት ኢሬቻ ላይ ለመታደም የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተሻለ መልኩ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተደረገው ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት መጥተው ከህዝቡ ጋር ያለውን ትስስር ከማጠናከር ባሻገር "አገር ውስጥ ያሉ ለውጦችንም ማየት እንዲችሉ እድል ይፈጠራል" ብለዋል።
በተጨማሪም በዓሉን በጋራ ማክበር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላት የሁሉም በዓላት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኢሬቻ በዓል ላይ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ወይዘሮ ለሊሴ ዱጋ በበኩላቸው፤ ለኢሬቻ በዓል የሚመጣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ ኮሚሽኑ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በናፍቆት የሚጠብቀውና በጋራ የሚያከብረው በዓል መሆኑን አንስተው፤ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት በመምጣት ባህሉንና ማንነቱን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በተለይም ከቱሪዝም አኳያ አዳዲስ የሚጎበኙ ስፍራዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩልም የበራራ ዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
የቱሪዝም ስፍራዎችን ከመጎብኝት ባለፈ የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ በቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ ማበረታቻዎች እየተዘጋጁ መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኢሬቻ በዓል ምክንያት ወደ አገራቸው በመምጣት ልማቱን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።