በክልሉ የታለመውን ልማትና እድገት እውን ለማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል - ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የታለመውን ልማትና እድገት እውን ለማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል - ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ በክልሉ የታለመውን ልማትና እድገት እውን ለማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተደድሯ በ13ኛው የክልሉ ትምህርት ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት በክልሉ የታለመውን ልማትና እድገት ማሳካት የሚቻለው "እቅዱን የሚተገብር ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው"።
የትምህርት ጥራት ሊጓደል የቻለውም የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች በቅንጅት ባለመስራታቸውና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ክልሉን ወደ ተሻለ ልማትና እድገት ለማሻገር በተለይም ከመምህራንና ከዘርፉ አመራር አካላት የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስትም ለትምህርት ጥራት መሻሻል አስፈላጊውን የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በቁርጠኝነት እንደሚያከናወን ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋልዋክ ሮን(ዶ/ር) በበኩላቸው ከጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በመምህራን የተነሱትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
ያጋጠመውን የትምህርት ጥራት ስብራት ለማቃናት መምህራን፣ የተማሪ ወላጆች ጥምረትና የዘርፉ አመራር በሙሉ ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው በማስገንዘብ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ የትምህርት ጥራት መጓደል በዋናነት የመምህራን የአቅም ውስንነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመሰረተ ልማት፣ የግብዓትና ሌሎች ችግሮች ድምር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የተጠቀሱትን ችግሮች በመፍታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብርን ጠይቀዋል።
ጉባዔው ሲጠናቀቅ ተሳታፊዎች ባወጡት የአቋም መግለጫ እንዳመለከቱት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የህዝብን ተሳትፎ በማጠናከር ለመሥራት ቃል ገብተዋል።
እንዲሁም ህዝቡን በማስተባበር የመሰረተ ልማት፣ የግብዓትና ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል እንደሚሰሩም በአቋም መግለጫቸው አመላክተዋል።