ከቡና የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ከቡና የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዳማ ፤ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ):- ከቡና የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ምርትና ምርታማነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የቡናና ሻይ ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዓመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የቡና ምርት ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ ስፔሻሊት ቡናዎችን ወደ ውጭ በመላክ በዘርፉ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የቡናን ጥራት ከማስጠበቅና ከግብይት አኳያ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢኖሩም አገሪቷ ካላት እምቅ አቅም አንጻር በቡና ምርታማነት ላይ አሁንም ትኩረት የሚፈልጉ ሥራዎች አሉ ብለዋል።
ውጤታማ የሆኑ ሞዴል አርሶ አደሮች ዘንድ ያለው የቡና ምርታማነት ዕድገት አርሶ አደሩ ጋር ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን መረባረብ እንደሚገባ ነው ሰብሳቢው የገለጹት።
ምርትና ምርታማነቱን ለማሻሻልም የቡና ጉድጓድ ዝግጅት፣ ተከላና ያረጁ ቡና ጉንደላ፣ እንዲሁም በምርት አሰባሰብ ወቅት በባለሙያዎች የታገዙ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የመፍጠርና ግብዓቶችን ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በቡና ጥራት እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች የውጭ ምንዛሬ ገቢው መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል።
የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከመደበኛ የቡና ልማት ማስፋፊያ ጎን ለጎን ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ ያረጁ የቡና ጉንደላ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
ከቡና ልማት ባለፈ የሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው፤ ስትራቴጂው ውጤታማ እንዲሆን አምራች አርሶ አደሩን ያማከለ ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።