በዙሪክ በሚደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዙሪክ በሚደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30 /2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አትሌቶች ዛሬ በስዊዘርላንድ ዙሪክ በሚካሄደው ዳይመንድ ሊግ ይወዳደራሉ።
ተጠባቂው የ5000 ሜትር ሴቶች ውድድር ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ43 ላይ ይካሄዳል።
አትሌት እጅጋየሁ ታዬ፣ አትሌት ፎትዬን ተስፋይ፣ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ፣ አትሌት መልኬናት ውዱና አትሌት ገላ ሀምበሴ በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።
እጅጋየሁ፣ ፎትዬንና ፅጌ በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክለው መወዳደራቸው ይታወቃል።
በውድድሩ 15 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ15 በሚካሄደው የ3000 ሜትር ወንዶች ውድድር አትሌት አዲሱ ይሁኔና አትሌት መዝገቡ ስሜ ይወዳደራሉ።
ዛሬ ማምሻውን በሚደረገው ዳይመንድ ሊግ የተለያዩ የመምና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ይካሄዳሉ።
የዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ በእስያ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል።
ዙሪክ ውድድሩ የሚካሄድበት 14ኛ ከተማ ነው።
ውድድሩ መስከረም 3 እና 4 2017 ዓ.ም በቤልጂየም ብራስልስ ፍጻሜውን ያገኛል።
በ14ቱ ውድድሮች የተሻለ ነጥብ ያገኙ 32 አትሌቶች (በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ 16 አትሌቶች) ብራሰልስ በሚካሄደው የሁለት ቀናት የማጠቃለያ ውድድር ላይ መሳተፋቸውን እንደሚያረገግጡ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
በብራሰልሱ ውድድር የሚያሸንፍ እያንዳንዱ አትሌት የ30 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛል።
በተጨማሪም አትሌቶች (ከተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር) እ.አ.አ በ2025 በቶኪዮ በሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ።