2016 ዓ ም እንደ አገር መሻገር የተቻለባቸው በርካታ አቅሞች የተፈጠሩበትና ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
2016 ዓ ም እንደ አገር መሻገር የተቻለባቸው በርካታ አቅሞች የተፈጠሩበትና ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- የ2016ዓ ም እንደ አገር መሻገር የተቻለባቸው በርካታ አቅሞች የተፈጠሩበትና ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ገለፁ።
ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ ም የመሻገር ቀን ሲሆን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች ”በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተገልጿል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ዕለቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት የ2016 ዓ ም በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ሰርታለች ብለዋል።
በተለይም በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና በኢነርጂ ዘርፎች የእይታ ለውጥ ጭምር በማድረግ የተሰሩ ስራዎች የመናገር ትልቅ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ለአብነትም በስንዴ ልማት፣ በተኪ ምርቶች፣ በቱሪዝም መዳረሻ ልማትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ መግባት የዓመቱ የመናገር ዋና ዋና ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ አገር በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ በማጎልበት በአዲሱ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
ዓመቱ እንደ አገር መሻገር የተቻለባቸው በርካታ አቅሞች የተፈጠሩበትና ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑንም አንስተው፤ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ ም ይህንን ታሳቢ ባደረጉ ሁነቶች ይከበራል ብለዋል።