ቀጥታ፡

ስልጠናው ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ማዘመን የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ነው - ሰልጣኞች  

ደብረ ብርሃን ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- ስልጠናው አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን በመጠቀም ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ማዘመን የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ነው ሲሉ በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ  ስልጠና ላይ  እየተሳተፉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኝ መምህራን ገለጹ። 

"ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሀሳብ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ስልጠና ለቴክኒክና ሙያ አሰልጣኝ መምህራን እየተሰጠ ይገኛል። 

የደናባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህርት ዝናሽ ተሾመ እንዳሉት፤ ስልጠናው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትና በማላመድ የሚስተዋለውን የአቅም ክፍተትን የሚሞላ ነው።

ይህም በሰልጣኞች መካከል የሚስተዋለውን የክህሎትና እውቀት ክፍተት ማቀራረብ ከማስቻሉም በላይ አሰልጣኝ መምህራን በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው አቅማቸውን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በተለይም ስልጠናው ከውጭ የሚገቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የተመረቱ እቃዎችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት የሚያስጨብጥ ሆኖ እንዳገኙትም ተናግረዋል።


 

የይፋት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ደረጀ ዘነበ ስልጠናው ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቴክኒክና ሙያ ስልጠና የወጡ አዳዲስ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በውል በመረዳት የዘርፉን የለውጥ ጎዳና በእውቀት ላይ ተመስርተን ለመደገፍ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የመሐል ሜዳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህር ዘለቀ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ስልጠናው የመምህራን ሙያ ልማት ለማዘመንና ተቋማትን በማሻሻል ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ አማካሪና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ድረሴ እሸቱ እንዳሉት፤ ስልጠናው የአመለካከትና አስተሳሰብ መጓደሎችን ለማስተካከል ያግዛል።

ስልጠናው በማስተማር ስነ ዘዴ፣ በዲጅታላይዜሽን የስራ ፈጠራና ክህሎት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሰልጣኝ መምህራን በእውቀት ላይ ተመስርተው የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በስልጠናው ላይ ከ21 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ የተውጣጡ 735 ሰልጣኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ስልጠናው በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ እሳቤ፣ በስራ ፈጠራ ክህሎት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም