የምሥራቅ ዕዝ የተሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ተጋድሎና ብቃት እየተወጣ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ ዕዝ የተሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ተጋድሎና ብቃት እየተወጣ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ጅግጅጋ ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በአገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ የተሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ተጋድሎና ብቃት እየተወጣ ያለ ዕዝ መሆኑን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
"የምሥራቁ ጮራ የኢትዮጵያ ወታደሮች ነን" በሚል መሪ ሐሳብ የኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጅግጅጋ በሚገኘው ገርባሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤ የምሥራቅ ዕዝ በምስራቁ የአገሪቷ ክፍል የተሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ተጋድሎና በብቃት እየተወጣ ያለ ዕዝ ነው።
ምስራቅ ዕዝ በአገሪቷ የተሰጠውን ግዳጅ ከመወጣት ጎን ለጎን የአገር ልማትና ሰላም በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንዲሆን ታሪካዊ አስተዋጽዎ ያበረከተ መሆኑንም ገልፀዋል።
በሶማሌ ክልልም ሰላምን በማስጠበቅ ልማቱ እንዲፋጠን፣ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉና አምራች ፋብሪካዎች እንዲጎለብቱ የምሥራቅ ዕዝ የድርሻውን ማበርከቱን ተናግረዋል።
እንዲሁም የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ እና ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ዕዙ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን ማበርከቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን የማይወዱ የፀረ ሰላም ሃይሎችን ተግባርን እኩይ ተልዕኮ በማምከን አኩሪ ገድል መፈፀሙን ነው የገለጹት።
የምሥራቅ ዕዝ አሁንም ለአገር ሉዓላዊነትና ሰላም መስፈን የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ህዝቡም ከዕዙ ጎን በመሆን አገሪቷን ለማተራመስ የሚፈልጉ ሃይሎችን ተግባር ነቅቶ በመጠበቅ መታገል እንደሚገባውም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐሙድ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የአገር ሠላም በአስተማማኝና ጠንካራ መሠረት ጸንቶ እንዲቀጥል የአገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ምሥራቅ ዕዝ በተለይም ለክልሉ ሰላምና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረው፤ ይኸም የሚያኮራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንደ ትናንቱ ከምሥራቅ ዕዝ ጋር የሚያከናውነውን የሰላምና ልማት ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
በአገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው፤ የዕዙ አባላት በቀጣይ በላቀ የግዳጅ አፈጻጸም ተልዕኮዋቸውን ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በበዓሉ ላይ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ የዕዝ አዛዦች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የክልሉ የአመራር አካላትና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የምሥራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከነሐሴ 21 ቀን ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።