ቀጥታ፡

የበዓል ገበያ ዋጋው በሁሉም ምርቶች የተረጋጋ ነው - የአርባምንጭ ከተማ ሸማቾች

 አርባ ምንጭ ፤ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፦የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል ገበያው በሁሉም ምርቶች የተረጋጋ ነው ሲሉ የአርባምንጭ ከተማ ሸማቾች ገለጹ።

የ2017 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባምንጭ ከተማ ሸማች ማህበረሰብ ገበያው በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ የተረጋጋ ነው ብለዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ በላቸው ጉተማ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ይፋ ካደረገበት ማግስት ጀምሮ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ በወሰደው እርምጃና ባመቻቸው አማራጭ ገበያዎች የሸቀጦች፣ የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ዋጋ ወደ ነበረበት መመለሱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው ገበያ እና ከአካባቢው በሚገቡ የፍጆታ እቃዎች ሁሉንም የምንፈልጋቸውን ቁሳቁሶች በተረጋጋ ሁኔታ እያገኘን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የፍየልና የበሬ ዋጋም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየና ተመጣጣኝ እንደሆነም አቶ በላቸው በአስተያየታቸው አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ማህበረሰብ ክፍሎች ገበያው ጥሩ መሆኑንም አክለዋል።

ሌላኛዋ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት ታምራት በበኩላቸው ገበያ ላይ የምርት አቅርቦት እጥረት አለመኖሩን ጠቅሰው፤ መንግሥት ባመቻቸው የሰንበት ገበያ ላይ የሚፈልጉትን ዕቃ ከመደበኛ ገበያው በቅናሽና በተመጣጣኝ እያገኘን ነው ብለዋል።

በመደበኛ ገበያ ላይ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 70 ብር እንደነበር ጠቅሰው፤ እሳቸው ግን ከአማራጭ የሰንበት ገበያ በ50 ብር ሂሳብ መሸመታቸውን በማከል።

ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ አንድ ሊትር ዘይት እስከ 300 ብር ሲሸጥ እንደነበረ ጠቅሰው፤ በተቀደረገው የቁጥጥር ስራ ዋጋው መውረዱንና በ220 ብር ሂሳብ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ከግብርና ምርቶች አኳያም ከመደበኛ ዋጋው ውጭ ባልተገባ መንገድ ጭማሪ የተደረገበት ምርት አለመኖሩን ጠቅሰው፤ በዚሁ መሠረት በመሸመት ላይ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ትዕግስት አክለውም መንግስት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ እንዲሁም አማራጭ የሰንበት ገበያን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን ሰይድ በበኩላቸው ለዘመን መለወጫ በዓል ከግብርና ምርት እስከ ፋብሪካ ምርት እንዲሁም ከዶሮ እስከ ቁም እንስሳት ድረስ በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ላይ ጭማሪ አለመኖሩን አስረድተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ምርትን ለማሸሽና የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሞከሩ አካላት መኖራቸውን አውስተው፤ በተደረገው የተቀናጀ ክትትልና በተወሰደው እርምጃ መሠረት ወደነበረበት መመለሱን ገልጸዋል።

በዚሁ ሂደት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ጭማሪ ባደረጉ 166 የንግድ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 110 የንግድ ድርጅቶችን የማሸግ፣ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ30ዎቹ ላይ የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም 26 የሚሆኑት ደግሞ በህግ አግባብ እንዲጠየቁ በማድረግ የእርምት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርም ከአርባምንጭ ከተማ ግብርና፣ ከህብረት ሥራና ከኢንተርፕራይዝ ተቋማት ጋር በመቀናጀት 10 ሸማቾችና ሶስት ዩኒየኖች ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸዋል።

አቶ ተመስገን አክለውም ህብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ የሰንበት ገበያዎች ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ የገበያ መረጋጋት እየሰፈነ መጥቷል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም