በከተማው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ስራ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በወልዲያ የተማሪ ወላጆች ገለጹ

ወልዲያ ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በወልዲያ ከተማ ለአዲሱ  የትምህርት ዘመን  ስራ ስኬተማነት ልጆቻቸውን በወቅቱ ከማስመዝገብ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን  ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን  በከተማው  የተማሪ ወላጆች ገለጹ።

በወልዲያ ለአዲሱ ዓመት ትምህርት ዘመን ስራ ውጤታማነት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማው አስተዳዳር ትምህርት መምሪያ  አመልክቷል። 

በከተማው የመልካ-ቆሌ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪ ወላጆች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ደስታ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቱ የማስተማር ስራ የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ ማደረጋቸውን አስታውሰዋል። 

''ትምህርት ቤቶች የህብረተሰቡ ናቸው፤ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢም ሆነ በውጪ ያላቸውን እንቅስቃሴ የመከታተልና ግድፈት ሲገኝ ማረም ዋናው ስራችን ነው'' ብለዋል። 

በአዲሱ ዓመት የመማር ማስተማር ስራ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምዝገባ ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆናቸውንና ድጋፋቸውንም አጠናክርው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

"የአምናውን ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት ዘንድሮም ይበልጥ በማጠናከር የድርሻችንን እንወጣለን" ያሉት ደግሞ በእቴጌ ጣይቱ ብጡል አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጃቸውን ሲያስመዘግቡ የነበሩ ወላጅ ወይዘሮ ወርቅነሽ አባተ ናቸው። 

በከተማው ለሚከናወነው የመማር ማስተማር ስራ ውጤታማነት ልጆቻቸውን በወቅቱ ከማስመዝገብ ባለፈ ሌሎችም ወላጆች በተመሳሳይ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ እየቀሰቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አስራት በሪሁን በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ ለ2017 የትምህርት ዘመን 25 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

እስካሁን ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በተደረገ ጥረትም ምዝገባው በተሳካ ሁኔታ ቀጥሎ እንዳለ ተናግረዋል።

ለመማር ማስተማር ስራ ስኬታማነትም 54 ሺህ 569 የመማሪያ መፅሃፍትና  ሌሎችም ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያገለግሉ ግብአቶች ዝግጁ መደረጋቸውን አስረድተዋል። 

እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል በተደረገ እንቅስቃሴም 28 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መሰናዳታቸውንም  አስታውቀዋል። 

የአዲሱ የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ ባሻገር የትምህርት ተቋማትን  ደረጃ በማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በወልዲያ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው  ያሉ 37 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ  ከትምህርት መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም