ባንኩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመደገፍ ከ150 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመደገፍ ከ150 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አገኘ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው አረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚውል 151 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማጽደቁን የአፍሪካ ልማት ባንክ ማስታወቁን ዥንዋ ዘገበ።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የሚደገፈው ይኸው ፕሮግራም "በአፍሪካ ቀንድ ለምግብና ለኑሮ ተስማሚ የአየር ንብረት ለውጥን መገንባት" የሚለው የባንኩ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ በጅቡቲ፣ በሶማሊያ፣ በኬኒያ፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አመልክቷል።
የአፍሪካ ልማት ባንክን ጠቅሶ እንደዘገበው "አዲሱ የገንዘብ ድጋፍ ማኅበረሰብ ተኮርና የሥርዓተ-ፆታ መመጣጠንን የሚቋቋም መፍትሄዎችን ይደግፋል" መባሉን ዥንዋ ዘግቧል።
ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ተግባራትን የአየር ንብረት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽነት፣ ታዳሽ ኃይል፣ የህብረት ስራ ማህበራት አቅም ግንባታ፣ አግሪ ቢዝነስ እና የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት፤የብድር፣የአየር ንብረት አገልግሎት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች፣ እና የኢንሹራንስ የመረጃ ጠቋሚ ጉዳዮችን ማሻሻል የሚሉት መፍትሄዎችን እንደሚረዳ ባንኩ መግለጹን ዘገባው ጠቅሷል።
የባንኩ የግብርና እና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዳይሬክተር ማርቲን ፍሬጌን የአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።
የአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ ድጋፍ ማሰባሰብ የአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና ቀጣይነት ያለው የግብርና ሥርዓትን በአፍሪካ ቀንድ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፣በዚህም በድራችን በጣም ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች በአንዱ የምግብ ዋስትናን ያሻሽላል ብለዋል ሲል ጠቅሷል።
ለፕሮግራሙ ከጸደቀው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 90 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሲሆን የ60 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ብድር መሆኑን ዥንዋ በዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በ2025 በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምረው ድጋፍ እንደሚያስተዳድርና ፕሮግራሙን እንደሚቆጣጠርም ማስታወቁንም ዘገባው ጠቅሷል።
የአፍሪካ ቀንድ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ያልተስተካከለ የዝናብ ስርጭት፣ለሙቀት መጨመር፣ ለድርቅና ጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ መሆኑን የአፍሪካ ልማት ባንክ ማመልከቱን ዘገባው አንስቷል።
የአየር ንብረት ለውጥ ለሰው፣ ለእንስሳትና ለሰብልና በሽታዎች መጨመርና ለየመሬት መራቆትን በማባባስ ምርታማነትን እንዲቀንስ ማድረጉንም ባንኩ መግለጹን አንስቷል።