በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ የሚውል ሰብል ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ እየለማ ነው

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለውጭ ገበያ የሚውል ሰብል ከ2 ሚሊዮን ሄክታር  በሚበልጥ መሬት ላይ  እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በራስ አቅም ለመሸፈንና ለውጭ ገበያ የሚውል ምርቶችን በብዛትና ጥራት ለማሳደግ ክልሉ የድርሻውን ለመወጣት ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን የግብርና ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ለዚህም በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ2  ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚሆን ሰብል እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሚለማው  መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታሩ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን  አኩሪ አተር፣ ስንዴና ጥጥ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።


 

ቀሪው  መሬት ደግሞ ለውጭ ገበያ የሚውል ሰሊጥ፣ ቦሎቄና ማሾ የመሳሰሉ የሰብል ዓይነት መሆኑን አመልክተዋል።

ከሚለማው መሬት   ከ68 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት መኖር  ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝና  የታቀደውን ምርት ማሳካት እንደሚቻል አስረድተዋልል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ተሾመ ይቴ በበኩላቸው፤በመኽሩ ወቅቱ 880 ሄክታር መሬት ላይ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለውጭ ገበያ በሚውል ሰብል በማልማት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 


 

እያለሙ ካሉት የሰብል ዓይነት መካከል አኩሪ አተር፣ ሰሊጥና  ጥጥ እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ ሰብሉን ከአረምና ተባይ የመከላከል ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል  በ2016/2017 የምርት ዘመን አጠቃላይ በተለያየ ሰብል ከለማው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ169 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት  እንደሚጠበቅ ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም