እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 30/2016(ኢዜአ)፦እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ መሆኑን  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ። 

ኢትዮጵያን የመሰለ ድንቅና እምቅ የመበልፀግ አቅም ያላት ሀገር ተችሮን ለእርዳታ እጃችንን የምንፀውትበት ጊዜ ይበቃል ብለን እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አደም ልመናን ተጠይፎ እጅን እና እግርን አስሮ ከሚይዝ የተረጂነት እሳቤ ነፃ የሆነ ማህበረሰባዊ ውቅር ገንብተን ፣በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን አረጋግጠን፣ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመጎናፀፍ እንድንችል እቅድ ነድፈን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።

አላማውን በተሟላ ደረጃ ለማሳካት በየደረጃው ካለው አስፈፃሚ እና ፈፃሚ አካል ጋር የጋራ መግባባት ፈጥረን፣በሁሉም ክልሎች ከ10.6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለሀገራዊ ሉዐላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ መድረኮች በማካሄድ ከህብረተሰባችን ጋር የጋራ መግባባትን ፈጥረን፣ እንዲሁም አብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን አዋቅረን ወደ ስራ ተገብቷል።

በዚህም መነሻነት ሕዝባችን በአርበኝነት ስሜት ልመና በቃኝ ብሎ እንዲነሳና ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ነፃነትን መጎናፀፍ ይገባናል የሚል ቁጭት እንዲፈጠርበት ተደርጓል ነው ያሉት።

እንደሀገር ሊኖረን የሚገባውን የፖሊሲ ነፃነት እና ተፅእኖ አልባ የሉአላዊነት ህልውና መጎናፀፍ የምንችለው ክብራችንን ለሚሰፈርልን ስንዴ መስዋእት አድርገን ካላቀረብን ብቻ እንደሆነና ከተረጂነት ለመላቀቅም ብቸኛው መፍትሄ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ ሕዝባችን ተረድቶታል።

ይህንን መነሻ በማድረግም በግብርናው ዘርፍ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በሌማት ትሩፋት፣በምግቤን ከጓሮዬ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎችም የልማት መርሃ ግብሮች የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት ስር የሰደደ የልመና እና የተረጂነት እሳቤን ከማህበረሰባችን የሞራል መዝገበ ቃላት ውስጥ ለመፋቅ መንቀሳቀስ ይኖርብናል።

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንድንችል የመንግስት የልማት ፕሮግራሞችን አቀናጅተን ተግባራዊ በማድረግ፣ በአንዳንድ ክልሎች የተጀመሩ ለምሳሌነት በኦሮሚያ ክልል "ቡሳ ጎኖፋን" የመሰሉ የህብረተሰቡ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት፣ በችግር ጊዜ ለወገን የመድረስ ባህልን የሚያሳድጉ እሳቤዎችን፣ ተቋማትንና ተግባራትን በማዳበር፣ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በአግባቡ ለይቶ ድጋፉን በራስ አቅም ለማቅረብ የሚያስችል ስራ በመስራት እና በቂ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያዎችን በማከማቸት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሙሉእነት ልንሸጋገር ይገባል።

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በደም የተከበረው ሉአላዊነታችንን በላባችን በማፅናት ከተረጂነት በመላቀቅ በራሳችን የምንቆምበትን አውድ መፍጠር ትውልዳዊ ግዴታችን ነውና ለአላማው ግብ መምታት ሁላችንም የሚጠበቅብን ኃላፊነት መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም