288 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፤ ነሔሴ 30/ 2016 (ኢዜአ)፡- 288 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከነሀሴ 17 ቀን እስከ 23/2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 244 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 43 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የውጭ፤ በድምሩ 287 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የመኪና መለዋወጫ፣የግንባታ ግብዓቶች፣ ወርቅ፣ የምግብ ዘይት፣ የቁም እንስሳት፣የጦር መሳሪያ እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዋሽ፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 81 ሚሊዮን፣ 56 ሚሊዮን እና 37 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ አስር ተጠርጣሪዎች እና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝብ ምስጋና ማቅረቡን ከኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም