የጳጉሜን ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል - የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የጳጉሜን ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል - የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ)፦አምስቱን የጳጉሜን ቀናት በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያየ ዝግጅትና ሥያሜ በድምቀት ለማክበር የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የ2017 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ አምስት የጳጉሜን ቀናት አከባበር ዝግጅትና ስያሜን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ2017 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ ብለዋል።
የጳጉሜን ወር ቀናት በኢትዮጵያዊያን የዘመን አቆጣጠር አሮጌውን ዘመን በመሸኘት የታለፉ ሂደቶችን በመገምገም በአዲስ ዕቅድና ተስፋ አዲሱን ዘመን ለመቀበል መሻጋሪያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በለውጡ ማግሥትም መንግስት የጳጉሜን ቀናትን ስያሜ በመስጠት የዜጎችን አንድነት፣ አብሮነትና አገራዊ ሉዓላዊነት ማጠናከር በሚያስችሉ ሁነቶች ሲከበሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም የአሮጌ ዘመን ስኬቶችን በአዲስ ዓመት በማስቀጠል የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፍትሔ ስልት በመቀየስ ተቋማትና ማኅበረሰቡ ለበለጠ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ በሚያደርግ ዝግጅቶች ሲከበሩ ቆይቷል ብለዋል።
ዘንድሮውም የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ አምስት የጳጉሜን ቀናት ግንዛቤን በሚፈጥር ስያሜና መልዕክት በደምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠለ፣ ተግዳሮቶችን በመቅረፍና በአዲሱ ዓመት የታቀዱ አገራዊ ትልሞችን በላቀ ደረጃ ለመፈጸም መነሳሳትን ለመፍጠር በማለም ቀናቱ እንደሚከበሩ ተናግረዋል።
በዚህም አምስቱ የጳጉሜን ቀናት የመሻገር፣ የሪፎርም፣ የሉዓላዊነት፣ የኅብርና የነገ ቀን በሚሉት ሥያሜዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት የሚከበሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
አምስቱ የጳጉሜን ቀናትም በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳድሮች፣ በፌዴራል ተቋማት፣ በውጭ አገራት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች፣ ቆንፅል ጽሕፈት ቤቶችና በማኅበረሰቡ ዘንድ በድምቀት ይከበራሉ ብለዋል።
"የመሻገር ቀን" የሚል ስያሜ በተሰጣት የጳጉሜን-1 ቀንም በሀገር አቀፍ ደረጃ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች" በሚል መሪ ኃሳብ በለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎችን በመዘከር ኢትዮጵያ መሻገሯን የሚታይበት ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
ጳጉሜን-2ም “የሪፎርም ቀን" በሚል ስያሜ “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት" በሚል መሪ ኃሳብ በዘመናዊ የተቋማት ግንባታ የአገልጋይነት ስሜትን በማጉላት ኢኮኖሚያዊ ስብራትን ለመጠገን ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት ይሆናል ብለዋል።
ጳጉሜን-3 “የሉዓላዊነት ቀን" በሚል ስያሜ “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ተከብሮ የሚውል መሆኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።
በዚሁ ጊዜም በለውጥ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተገዳደሩ ፈተናዎችን በመቋቋም የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማፅናት የተሰሩ ሥራዎች ታስበው እንደሚውሉ ገልጸዋል።
በዕለቱም ከቀኑ 6፤00 ስዓት ላይ የመንግሥትና በግል ተቋማት የሰንደቅ ዓላማ በመስቀል ሁሉም ሰው ባለበት ቆሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሚዘምርበት ሥነ-ሥርዓት እንደሚኖር አስገንዝበዋል።
ጳጌሜን-4ም “የኅብር ቀን" በሚል ስያሜ “ኅብራችን ለሰላማችን" በሚል መሪ ኃሳብ የኢትዮጵያዊያን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት፣ መልክዓምርድና ምኅበራዊ መስተጋብር በሚያንጸበርቅ መልኩ ታስቦ እንደሚውል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያን ኅብረ በሔራዊ ማንነት የጥንካሬያች መሰረት በመሆኑ በዕለቱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተንጸባርቆ የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
“የዛሬ ትጋት፣ ለነገ ትሩፋት" በሚል መሪ ኃሳብ ታስቦ የሚውለው ጳጉሜን-5ም “የነገ ቀን" በሚል ስያሜ የኢትዮጵያዊያንን መፃኢ ተስፋ ታሳቢ ባደረገ ዝግጅት ተክበሮ ይውላል ብለዋል።
በዕለቱም የአገር ግንባታ ስኬቶችና በሀገር ግንባታ ሂደት በሚያስገነዝብ መልኩ የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች የሚዳሰሱበት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የ5ቱ ቀናት የአከባበር ሁኔታም የየቀናቱ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በየወቅቱ ዝርዝር መልዕክቶችን በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ለሕዝብ ይፋ እየተደሩ እንደሚሄድ አስታውቀዋል።